ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ባከናወነችው ውጤታማ ስራዎች የሀገር ውስጥ መድሃኒት አቅርቦትን ማሳደግ ችላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ባከናወነችው ውጤታማ ስራዎች የሀገር ውስጥ መድሃኒት አቅርቦትን ማሳደግ ችላለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ባከናወነችው ውጤታማ ስራዎች የሀገር ውስጥ መድሃኒት አቅርቦትን ማሳደግ መቻሏን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።
19ኛው ዓለም አቀፍ የህክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀምሯል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች ብለዋል።
ከእነዚህ ውጤታማ ተግባራት መካከል የጤና ተቋማት መሠረተ ልማትና ተደራሽነት፣ የህክምና መሳሪያ፣ የመድሃኒት አቅርቦትና የሙያተኞች አቅም ግንባታ ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም የጤና አገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂያዊ አሰራሮችን ተደራሽ በማድረግ ዘርፉን ለማሻሻል ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
ለዚህም ከዘርፉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት የሚተሳሰሩበት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በአራት ዓመት ብቻ የሀገር ውስጥ መድሃኒት አቅርቦትን ከ8 በመቶ ወደ 44 በመቶ ከፍ ማድረግ ችላለች ነው ያሉት።
ይህም አፍሪካ በ2040 እ.ኤ.አ 60 በመቶ የሚሆን የመድሃኒት አቅርቦቷን በራሷ አቅም እንድትሸፍን ለሚደረገው ጥረት መነሻ ይሆናል ብለዋል።
ጉባኤው በዘርፉ የሚከናወኑ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ለማጠናከርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ሚኒስትሯ ገልጸዋል።