ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለዓለምና ለቀጣናው ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ላለፉት ሰባት አሥርት ዓመታት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ በመሳተፍ ለዓለም አቀፍና ለቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቷን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል ገለጹ።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ዘርፍ የዓለምንና የቀጣናውን ሰላም በመጠበቅ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት የበኩሏን ሚና ስትወጣ መቆየቷን ጠቅሰዋል፡፡

የኢፌዴሪ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋምና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በጋራ ባዘጋጁት መድረክ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ሥርዓት ለውጥና በባለብዙ ወገን ትብብር መዳከም ተግዳሮቶች ውስጥ የሰላም ማስከበር ሚናዋን የምታስቀጥልባቸው ስትራቴጂዎች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።

ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን በመድረኩ ላይ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ከኮሪያ ጦርነት ጀምሮ በሰላም ማስከበር ረጅም ጊዜ የቆየ አኩሪ ታሪክ ያላት ሀገር ስትሆን፣ ይህም ለዓለም አቀፍና ለሀገራዊ ሰላምና ደኅንነት ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያ አኩሪ ታሪኳን ለማስቀጠል ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ሁኔታ በጥንቃቄ በመገምገም ተግባራዊ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

የኢፌዴሪ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋም አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ገዛኸኝ ፈቃዱ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ከሰባት አሥርት ዓመታት በላይ ከ180 ሺህ በላይ የሰላም አስከባሪዎችን ወደ ተለያዩ ሀገራት ማሰማራቷን ገልጸዋል።

ተሳትፎዋም ከኮሪያ ጦርነት ጀምሮ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ መቀጠሉን ጠቅሰው፣ ይህ አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ ለጋራ ደኅንነት፣ ለቀጣናዊ መረጋጋትና ለዓለም አቀፍ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አመልክተዋል።

ሚናውን ለማስቀጠልም ዝግጁነትን ማጠናከር፣ አቅምን ማዘመንና ዘላቂ አጋርነት መገንባት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ አዛዥ ተወካይ ሠራው ደማስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት ወታደሮቿን በማሰለፍ ለዓለም አቀፍና ለቀጣናዊ ሰላም የበኩሏን ሚና ስትወጣ መቆየቷን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ኅብረት የፈረንሳይ የመከላከያ አታሼና የፈረንሳይ አምባሳደር ተወካይ ኮሎኔል ዳሚየን ሲፕሪክ በሳይበር ጥቃት፣ በመረጃ ጦርነት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎትና በድሮኖች አጠቃቀም እየተለወጠ የመጣው የትጥቅ ግጭቶች ባህሪ የሰላም ማስከበር ሥራን ይበልጥ ውስብስብ እያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅም አዳዲስ አካሄዶች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም