ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ እና የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ እና የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም እየወሰደች ያለችውን ተግባራዊ እርምጃ አጠናክራ እንደምትቀጥል የኮፕ 32 ፕሬዝደንሲ ቡድን አባል አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።

“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።

በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን እየተሳተፈ ይገኛል።

የኮፕ 32 ፕሬዝደንሲ ቡድን አባል አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) የኮፕ ፕሬዝዳንት ቡድን ጨምሮ የኢትዮጵያ ልዑክ በኮፕ 31 እና በሌሎች ጉባኤዎች ላይ የኢትዮጵያ አቋም ለጉባኤው የማሳወቅ እና የማስተባበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት የጋራ መኖሪያ የሆኑትን አፈር፣ ውሃ እና አየር ከጉዳት ለመጠበቅ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሪዮ ኮንቬንሽን አማካኝነት ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን በማንቀሳቀስ እና አዳዲስ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ረገድ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናት ብለዋል።

እንደ ኢኮኖሚ፣ ጤና እና ኢነርጂ ያሉ መሰረታዊ ፖሊሲዎች ከአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ጋር በሚጣጣም መልኩ እንዲቀረጹ እና ተግባራዊ እንዲሆኑ ሰፊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማስተባበር ረገድ አርአያ የሚሆኑ እና ጠንካራ መሠረት የያዙ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በቀጣይም አረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግና የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የሚደረጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም