ቀጥታ፡

ዘመናዊ አሰራር ግብራችንን በወቅቱና በአግባቡ እንድንከፍል አግዞናል - የሐረሪ ክልል ግብር ከፋዮች

ሐረር፤ ሕዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦የሐረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ አገልግሎት አሰጣጡን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማገዙና ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋቱ ግብራቸውን በወቅቱና በአግባቡ እንዲከፍሉ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ግብር ከፋዮች ተናገሩ።

በክልሉ በ2019 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑም ተመላክቷል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የክልሉ ግብር ከፋዮች እንዳሉት፣ ቢሮው ቀደም ሲል በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን መፍታቱ ግብራቸውን በአግባቡ እንዲከፍሉ አግዟቸዋል።

ለተለያዩ ድርጅቶች ግብርን በወቅቱና በአግባቡ እንደምትከፍል የተናገረችው ግብር ከፋይ ሃና መንግሥቴ፣ ይህም ከቅጣት እና ከተለያዩ ችግሮች እንደሚታደጋት ተናግራለች።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የሚሰጠው አገልግሎት አሰጣጥ እየዘመነ መምጣትና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር መተግበሩ፣ ቀደም ሲል ግብር ለመክፈል ሲመጡ ይገጥማቸው የነበረውን መጉላላት ማስቀረቱን ገልጸለች።

ቢሮው ባስቀመጠላቸው የግብር ክፍያ መፈጸሚያ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ እየከፈሉ እንደሚገኙና በዚህም ደስታ እንደሚሰማቸው የተናገሩት ደግሞ ግብር ከፋይ አቶ ብሩክ ውብዬ ናቸው።

በተለይ ቢሮው ያከናወነው የደንበኛ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥራዎች ለግብር ከፋዩ እርካታን እያጎናጸፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ላለፉት ዓመታት ግብሩን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ግዴታውን ሲወጣ መቆየቱን የተናገረው ሌላው ግብር ከፋይ ሔኖክ ደጀኔ ነው።

በተቋሙ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ የመጣው የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ቀደም ሲል በግብር አሰባሰብ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ከማስቀረት ባለፈ ግብርን በወቅቱ ለመክፈል መነሳሳት መፍጠሩን ተናግሯል።

የግብር ከፋዩን ቅሬታ የፈቱ ዘመናዊ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን የተናገሩት ደግሞ በሐረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ የገቢ አወሳሰን ባለሙያ ከሪማ አብዱለዚዝ ናቸው።

ቴክኖሎጂው ቀደም
ሲል በግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ሲነሣ የነበረውን ቅሬታ በመፍታት ቀልጣፋ አሠራር ለመዘርጋት ማስቻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የገቢ አሰባሰብ እና ክትትል ዳይሬክተር ሙና ሁሴን እንዳሉት፣ በክልሉ በ2019 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው።

ዕቅዱን ለማሳካትም አዲሱን የታክስ ስሌት ተግባራዊ የማድረግ ሥራዎች እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራዎች በትኩረት ተከናውነዋል።

አገልግሎት አሰጣጡን ከማሻሻ
ል ባለፈ ግብር ከፋዩ ግብሩን አውቆ በታማኝነት እንዲከፍል የተከናወኑ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች በገቢ አሰባሰብ ሂደት እና ውጤት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል።

በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፣ በቀጣይም ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አንጻር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የቢሮው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ከ1 ቢሊዮን 202 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 119 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም