ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት እና የካርበን ልቀት ቅነሳ ስኬቶች የዓለምን ትኩረት ስበዋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት እና የካርበን ልቀት ቅነሳ ስኬቶች የዓለምን ትኩረት መሳባቸውን የኮፕ 32 የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንሺያል ቡድን አባል አቶ ገብሩ ጀምበር ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።

“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።

በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የኮፕ 32 የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንሺያል ቡድን አባል አቶ ገብሩ ጀምበር ሀገሪቱ በካርበን ገበያ እና በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው ተጨባጭ ውጤት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት መሳቡን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በፓሪስ ስምምነት መሰረት ባቀደችው የልቀት ቅነሳ ግብ መሰረት፣ እስከ 2035 ከ70 በመቶ በላይ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እና በ2050 ወደ ዜሮ ልቀት (Net-Zero) ለመድረስ የገባችውን ቃል በተግባር እያሳየች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን የተከለቻቸው 56 ቢሊዮን ችግኞች እና በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ለዓለም አቀፍ የልቀት ቅነሳ ግቦች ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ ሰፊ ስራዎች በኮፕ 32 የኢትዮጵያ ፓቪሎን ላይ በምስልና በቪዲዮ እየቀረቡ ሲሆን፣ በርካታ የዓለም ሀገራትና ድርጅቶች ኢትዮጵያ የምትናገረውን በተግባር የምትፈጽም ሀገር መሆኗን በመገንዘብ አብረዋት ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በደን ልማት የተሰሩ ስራዎችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመለካት የሚያስችል የ"ኤም.አር.ቪ" (MRV) ማዕቀፍ በዘመናዊ የሳተላይት መረጃዎች በማዘመን ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የግብርና፣ ደን፣ ካርታ ስራ እና ስታቲስቲክስ ተቋማት በጋራ በመቀናጀት የደን ሽፋን ለውጦችን በከፍተኛ ጥራት በመለካት ወደ ካርበን ገበያ ለማስገባት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በድርድር መድረኮች ላይም የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ታዳጊ ሀገራትን (LDC) እና የአፍሪካ ቡድንን በመወከል የካርበን ገበያ ድርድሮችን በንቃት በመምራት ላይ መሆኑን ነው የጠቆሙት ።

በየሰዓቱ ከ30 በላይ በሚካሄዱ የድርድር ክፍሎች ውስጥ የኢትዮጵያ ተወካዮች በመገኘት፣ የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስጠብቁ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ በከፍተኛ ኃላፊነት እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከካርበን ንግድ የሚገኘውን ገቢና የሙያ ድጋፍ ለአካባቢው ማህበረሰብ በፍትሃዊነት ለማከፋፈል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እና የምዝገባ ስርዓት (Registry) በማዘጋጀት ለግሉ ዘርፍና ለዓለም አቀፍ አጋሮች ምቹ ሁኔታን መፍጠሯን አብራርተዋል።

ይህ ቁርጠኝነት በታዳጊ ሀገራት ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በከፍተኛ ትኩረት ከተያዘ ምን ያህል ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ለዓለም ያሳየ መሆኑንም አንስተዋል።

በአጠቃላይ በኮፕ 31 ጉባኤ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በባለሙያዎች ደረጃ ሲካሄዱ የቆዩት የካርበን ገበያና የሙቀት አማቂ ጋዞች ድርድሮች አበረታች ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጉባኤው ወደ ሚኒስትሮች ደረጃ እየተሸጋገረ ሲሆን፣ በቀጣይ ቀናትም ኢትዮጵያንና ታዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ገንቢ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም