ቀጥታ፡

የሥራ ፈጠራ ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት

የሥራ ፈጠራ ሳምንት (Global Entrepreneurship Week - GEW) በየዓመቱ በህዳር ወር አጋማሽ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ (ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ200 በላይ ሀገራት ውስጥ) የሚከበር ትልቅ የስራ ፈጠራ ንቅናቄ ነው።

የሳምንቱ መከበር ዋና ዓላማዎችም የስራ ፈጠራ ባህልን ማሳደግ፡ በተለይ ወጣቶችና ሴቶች አዳዲስ የንግድ ሀሳቦችን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ማነሳሳት፣ ግንኙነት መፍጠር፣ ስራ ፈጣሪዎችን ከባለሀብቶች (Investors)፣ ከአማካሪዎች (Mentors) እና ከመንግስት አካላት ጋር ማገናኘት፣ እውቀትና ክህሎት ማጋራት ሲሆኑ፤ በዚሁም ስለ ንግድ አመራር፣ ስለ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ስለ ገበያ ትስስር ስልጠናዎችን መስጠት ዋናዎቹ ናቸው። 

የዚህ አመት የዓለም አቀፉ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሳምንት (መሪ ሐሳብ "ግንኙነቶችን መፍጠር፣ እድገትን ማፋጠን" (Building Connections, Accelerating Growth) ወይም "አብሮ መገንባት" (Together We Build) በሚሉ ሐሳቦች ላይ ያተኮረ ነው።

በዓለም አቀፉ የሥራ ዕድል ፈጠራ አውታር (Global Entrepreneurship Network - GEN) የሚዘጋጀው  የሳምንቱ አከባበር የዘንድሮው መርሐ ግብር ትኩረት ከተደረገባቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል አንዱ የሥነ-ምህዳር ትስስር ነው ። ይህም ሥራ ፈጣሪዎችን ከባለሀብቶች፣ ከአማካሪዎች እና ከተመራማሪዎች ጋር በማገናኘት ጠንካራ የንግድ ሥነ-ምህዳር መፍጠር ነው። ሌላው የቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ሲሆን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አዳዲስ የንግድ ሐሳቦችን ማሳደግ ይሆናል። እንዲሁም አካታችነት ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ሲሆን፡- ወጣቶችን፣ ሴቶችን እና በገጠር አካባቢ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎችን በንግዱ ዘርፍ በስፋት ማሳተፍን የተመለከተ ነው። ሌላው ዘላቂነት ሲሆን ይህም የአካባቢ ጥበቃን እና አረንጓዴ ልማትን ያገናዘቡ የንግድ ሥራዎችን ማበረታታት ይሆናል።

ሳምንቱም ሀገር በቀል የፈጠራ ሐሳቦችን በማበረታታት እና የገበያ ትስስር በመፍጠር በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የልማት መስኮች፣ ኢኒሼቲቮች እና ኢንዱስትሪዎች የሚፈጠሩ የስራ እድሎች ሀገራዊ ስራ አጥነትን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

የስራ እድል ከሚፈጠሩባቸው ዘርፎች አንዱ ግብርና ሲሆን ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ከፍተኛውን የስራ እድል ይይዛል። ዝርዝር መስኮቹም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻ፣ የግብርና ግብዓት አቅርቦት፣ የዘር ብዜት እና የግብርና ምርቶች እሴት ሰንሰለት ናቸው። 

ሀገራዊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋትም የቤተሰብን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሳደግ የተጀመረ ኢኒሼቲቭ ሲሆን በዚህም ለወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የስራ እድል ተፈጥሯል። በዘርፉ የስራ እድል እየተፈጠረባቸው ካሉ መካከል የዶሮ እርባታ የእንቁላልና የስጋ፣ የወተት ላሞች እርባታና ወተት ማቀነባበር፣ የንብ ማነብ የማር ምርት እና የዓሳ እርባታ ዋናዎቹ ናቸው።

በተመሳሳይ አረንጓዴ አሻራ እና አካባቢ ጥበቃ ሲሆን ይህ ዘርፍም ወቅታዊ እና ቋሚ የስራ እድሎችን በመፍጠር ይታወቃል። በዘርፉ የሚፈጠሩ የስራ እድሎችም የችግኝ ማፍላት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች፣ የደን ጥበቃ እና የእንስሳት መኖ ልማት ናቸው።

ኢንዱስትሪ (ማኑፋክቸሪንግ እና ኮንስትራክሽን) ሌላው የስራ እድል የሚፈጠርበት ዘርፍ ሲሆን  የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ የስራ እድል ይፈጥራሉ። የዘርፉ ዋና የስራ መስኮች፦ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻ እና የህንጻ ግንባታ ይጠቀሳሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት ተቀርጾ ስልጠና እየተሰጠበት ያለው የኢትዮ ኮደርስና ዲጂታል ኢኮኖሚ ኢኒሼቲቭም በቀጥታ ስራ ከመቅጠር ይልቅ ወጣቶች በዓለም አቀፍ እና በሀገር ውስጥ የዲጂታል ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ስራ እንዲፈጥሩ ወይም እንዲቀጠሩ የሚያስችል ክህሎት ይሰጣል።

ዘርፉ በሶስት ዓመት ውስጥ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና በዲጂታል ማርኬቲንግ የማሰልጠን እቅድ ሲሆን፤ ይህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በርቀት እና በሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የስራ እድል እንዲያገኙ መንገድ ይከፍታል። ዋና የስራ መስኮችም ሶፍትዌር ማበልጸግ፣ ዳታ አናሊሲስ፣ ዲጂታል ግብይት እና የቢዝነስ ፕሮሰስ አውትሶርሲንግ ናቸው።

ሌላው ሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ሲሆን በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የተገነቡ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች (እንደ ገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች) ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ አነቃቅተውታል። ዋና የስራ መስኮቹም የሆቴልና ሪዞርት መስተንግዶ፣ አስጎብኚነት፣ የባህል እደ-ጥበብ ውጤቶች ሽያጭ እና የትራንስፖርት አገልግሎት ናቸው።

በየዓመቱ የሚከበረው የስራ ፈጠራ ሳምንት፣ ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የወጣት ኃይል ወደ ምርታማነት ለመቀየር እና የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መድረክ ነው።

በተለይም በሀገሪቱ እየተተገበረ ካለው የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይ እና የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ፣ ሳምንቱ የሚከተሉትን ቁልፍ ፋይዳዎች ያስገኛል፦

ወጣቶችና ምሩቃን "ስራ ጠባቂ" ከመሆን ይልቅ "ስራ ፈጣሪ" እንዲሆኑ የሚያነሳሱ የልምድ ልውውጦች እና ውይይቶች ይካሄዱበታል። አዳዲስ የንግድ ሀሳብ ያላቸው ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ከባንኮች፣ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ ከግል ባለሀብቶች እና ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን ዕድል ያመቻቻል። ሴቶች እና በክልል ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች በቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች አዳዲስ ፈጠራዎችን ይዘው እንዲወጡ የክህሎት ስልጠና እና የማማከር ድጋፍ እንዲያገኙ ያግዛል።

በአጠቃላይ የስራ ፈጠራ ሳምንት በኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ የስራ ፈጠራ ምህዳር ለመገንባት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እና ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን እንደ ዋነኛ አነቃቂ ኃይል ሆኖ ያገለግላል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም