ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ልማት አዲሱን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እያበሰረ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019(ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ልማት በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባን ሀገር በማነጽ አዲሱን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እያበሰረ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ኢትዮጵያ ከቡና መገኛነቷና የሰው ዘር ጥንታዊ ሀገረ ግንድ ታሪክ ምስክር ከሆኑት የሉሲና የሰላም ቅሪተ አካላት እስከ አረንጓዴ ዐሻራና የታዳሽ ኃይል የልማት እመርታ ድረስ ዓለምን እያስደመመች ነው።

ከጥንታዊ የሺህ ዘመናት ገናና ሥልጣኔና ቅርስ እስከ ዘመናዊ የከተማ ልማት፣ ከፓን-አፍሪካ አንድነት እሳቤ እስከ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ድሎቿ ድረስ የአህጉሪቷ የዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጓታል።

የኢትዮጵያ የታሪክ፣ የሥልጣኔ፣ የተፈጥሮ ሀብትና ዘመናዊ የልማት በርካታ መገለጫዎችን በአንድ ላይ በማሰናሰል በሰመረ ብሔራዊ ስትራቴጂ የወደፊት ርዕይዋን እየቀረጸች ትገኛለች።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የሰው ልጆች የዘር ሀረግ የሚመዘዝባት ምድረ ቀደምትና በመንግሥት አስተዳደር ቀዳሚ የሥልጣኔ ባለቤት ናት።

የኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት ገናና ሥልጣኔም በዓባይ ወንዝ ባለቤትነት፣ የሰው ዘርና የቡና መገኛነት፣ በዓድዋ ከተጎናጸፈችው ነጻነትና የብርቅዬ ሀብቶች መገኛነት የሚመነጭ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ለዓለም ያበረከተቻቸው ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶችና እሴቶች የምትታወቅባቸው ልዩ መገለጫዎቿ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ብዝኃ የኢኮኖሚ ልማት የሰጠው ትኩረትም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርን ያሰናሰለ አዲስ የሥልጣኔ ብርሃን መፈንጠቁን ተናግረዋል።

ይህም የዜጎችን ሕብረ ብሔራዊ ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛን የሚያስጠብቅ ፍትሐዊና አካታች ምኅዳር በመገንባት ወንድምና እህትማማችነትን በእጅጉ እያጎለበተ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንና የዜጎች የአብሮነት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላትም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ እየተከበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዜጎች የአብሮነት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላትም ሉዓላዊ አንድነቷ የተጠበቀችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት እየጣሉ መሆኑን አብራርተዋል።

የመደመር መንግሥት የብዝኃ ኢኮኖሚ ልማት ለቱሪዝም ዘርፍ የፈጠረው ዕድልም ታሪካዊ ሀብቶችን በመጠበቅ የሀገርን ውድ የቅርስ ሀብቶች መጠበቅ እያስቻለ ነው ብለዋል።

በተለይም የመደመር መንግሥት ለመንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርስ ልማትና ጥበቃ የሰጠው ልዩ ትኩረት ክብርን የሚያጎናጽፍ የትውልድ ግንባታ ትርክትን በማስረጽ የሀገርን ማንነትና መመኪያነት እንዲያገለግል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ይህም የኢትዮጵያን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ የተፈጥሮ ጸጋዎችና የሕዝብ እሴቶችም የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በአዲስ አበባ ጨምሮ የአጼ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት፣ የጅማ አባጅፋር፣ የሀረር ጀጎል ግንብና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶች ዕድሳት የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ አስቻይ የቱሪዝም ምኅዳር እንዲላበሱ ማድረጉን ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ልማት በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባን ሀገር በማነጽ አዲሱን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እያበሰረ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም አሰባሳቢና የወል ትርክትን የሚያንጽ ዐሻራን በማንበር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባ ኢትዮጵያን ታላቅነት እያበሰረ መሆኑን አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም