ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ከሞሮኮ ጋር ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦ በ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር  ኢትዮጵያ ከሞሮኮ ጋር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያከናውናል።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ በፕሪንስ ሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም ይካሄዳል።


ሀገራቱ ህዳር 3 2019 ዓ.ም በድሬዳዋ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ሞሮኮ 1 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ዩኑስ ኤል ባህራዊ በ29ኛው ደቂቃ ግቧን አስቆጥሯል።

በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ውጤቱን ለመቀልበስ ከሁለት እና ከዚህ በላይ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይኖርበታል።

በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ሞሮኮ ያቀናው ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ጨዋታው በሚደረግበት ፕሪንስ ሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም አድርጓል።

ተጫዋቾቹ በሙሉ ጤንነት እና ዝግጁነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በደርሶ  መልስ የሚያሸንፈው ሀገር ወደ መጨረሻው ዙር ማጣሪያ ያልፋል።

ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በግብጽ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ ግብጽን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ይሳተፋሉ።

በአፍሪካ ዋንጫው ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ ብሔራዊ ቡድኖች በቀጥታ እ.አ.አ በ2028 ሎስ አንጀለስ በሚካሄደው 34ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ይሳተፋሉ።

በውድድሩ አራተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን ከሌላ አህጉር አራተኛ ደረጃን ከያዘ ቡድን ጋር ለሚደረግ የጥሎ ማለፍ (Play-off) ጨዋታ ያልፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም