ኢትዮጵያ ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ከሞዛምቢክ ጋር ዛሬ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ከሞዛምቢክ ጋር ዛሬ ታደርጋለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦ በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አራተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከሞዛምቢክ ጋር ያካሂዳል።
የብሔራዊ ቡድኖቹ የምድብ 10 ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በባህር ዳር ስታዲየም ይከናወናል።
ሀገራቱ ህዳር 4 ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ 1 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ከነዓን ማርክነህ በ87ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል። ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ በማጣሪያው የመጀመሪያ ድሏን አግኝታለች።
ዋልያዎቹ በሶስት ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ከጨዋታው መልስ በባህር ዳር ዝግጅቱን አድርጓል።
የመጨረሻ ልምምዱንም ትናንት በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ማድረጉንና ተጫዋቾቹ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
በ60 ዓመቱ የሀገሯ ዜጋ ቺኩኒዮ ኮንዴ የሚመራው የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድንም የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በስታዲየሙ አድርጓል።
ሞዛምቢክ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
ጨዋታው ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምታደርገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።
ብሔራዊ ቡድኑ ካሸነፈ ሁለተኛ ደረጃን ከሞዛምቢክ ይረከባል።
ጋምቢያዊው ንፋሊ ጃርጁ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በተያያዘም ትናንት በምድብ 10 በተደረገ ጨዋታ ሴኔጋል ሱዳንን 4 ለ 2 በመርታት በ10 ነጥብ መሪነቷን አጠናክራለች።
ሱዳን በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።