ቀጥታ፡

በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን በመኸር እርሻ ከለማው ስንዴ ከ62 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

ሮቤ፤ ህዳር 08/2019(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል መልማቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ አካባቢ በምቹ የአየር ንብረቱ እና ለእርሻ ተስማሚ በሆነው ሰፊ ለም መሬቱ ምክንያት በኢትዮጵያ በስንዴ ምርት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ቀጣናዎች አንዱ ነው። 
 
አካባቢው ለረጅም ዓመታት የአገሪቱን የስንዴ ፍላጎት በመሸፈን ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል።

በቅርብ ዓመታትም በአካባቢው በኩታ ገጠም እርሻ አሰራር፣ በሜካናይዜሽን አጠቃቀም እና በምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ በተሰሩ ሰፋፊ ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል። 

ይህም አገሪቱ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የያዘችውን ሀገራዊ ግብ በማሳካት ረገድ ትልቅ መሠረት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በዞኑ በዘንድሮው የመኽር እርሻም በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር አጠቃላይ መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩ የስንዴ ልማት መሆኑ ተመላክቷል።

ከዚህም 62 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ ነው የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የገለጸው።
 
ከሰሞኑም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በዞኑ የሲናና እና አጋርፋ ወረዳ እየተከናወኑ ያሚገኙ የግብርና ልማት ሥራዎችን በመስክ ተመልክተዋል።

 
በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልገፋር ከማል እንዳሉት በዞኑ በዘንድሮ የመኽር እርሻ ከ80 በመቶ በላይ በሜካናይዜሽን በመታገዝ በተሻሻሉ አሰራሮች በመልማቱ የተሻለ ምርት ይገኛል ተብሎ ታቅዷል።

በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ቡድን አባላት በመስክ የተመለከቱት የዞኑ ሲናና ወረዳ ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ክላስተር እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

በስንዴ ልማቱም የግብርና ዘርፉን በማዘመን፣ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

ለዚህም የተሻሻሉ የሰብል ዘሮችንና ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ፣ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋፋትና የክላስተር እርሻን በማሳደግ የግብርና ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዞኑ በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ የሚገኙ ሁለንተናዊ ጥረቶችና የተገኙ ስኬቶች ይበልጥ በማስተዋወቅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጠናከር የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጉብኝት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሐሰን ከድርና ሼህ አህመድ አልይ በሰጡት አስተያየት የተሻሻሉ አሰራሮችና ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዘንድሮ የመኽር ወቅት ከሌሎች 15 የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በኩታገጠም በመደራጀት እያለሙ ከሚገኙት የስንዴ ልማት በሄክታር እስከ 60 ኩንታል እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ቡድን አባላቱ ጉብኝታቸውን በመቀጠል በዞኑ የሚገኙ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች መዳረሻዎችና የቱሪዝም የመስህብ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም