ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ውጤቶች በዓለም አቀፍ መድረክ አቀረበች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ውጤቶች በዓለም አቀፍ መድረክ አቀረበች
አዲስ አበባ ፣ህዳር 8/2019 (ኢዜ )፦አበቱርክ አንታሊያ እየተካሄደ በሚገኘው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) ላይ ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት እና የአየር ንብረት ተቋቋሚነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ያስመዘገበቻቸውን ተጨባጭ ውጤቶችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ይፋ አድርጋለች።
በCOP31 የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን በብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት “ከቤሌም እስከ አንታሊያ፦ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀትና የአየር ንብረት ተቋቋሚ ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያ ጉዞ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ከፍተኛ የግምገማ መድረክ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የልማት አጋሮች ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ከተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት አንዱ ሲሆን፤ በ2018 ዓ.ም ብቻ ከ8.2 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ መሆኑና መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተተከሉ ችግኞች አጠቃላይ ቁጥር ከ56 ቢሊዮን በላይ መድረሱ ተገልጿል።
በተጨማሪም የንጹህ ትራንስፖርት ሽግግርን በተመለከተ በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 144 ሺህ 429 መድረሱ ተመላክቷል።
የፖሊሲ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን በተመለከተም የካርቦን ገበያ አዋጅ መጽደቁ፣ የብሔራዊ የካርቦን መዝገብ ሥርዓት መዘጋጀቱ፣ እንዲሁም የአየር ንብረት መረጃ ማዕከል እና የተቀናጀ የክትትል፣ ሪፖርትና ማረጋገጫ ሥርዓት መዘርጋቱ እንደ ዋና ዋና ስኬቶች ተነስተዋል።
በመድረኩ የቀጣይ ዓመት ታላቅ ኃላፊነት የሆነው እና ኢትዮጵያ በ2027 በአዲስ አበባ የምታስተናግደውን የCOP32 ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ በብሔራዊ፣ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ዝግጅት እያደረገች መሆኗ ተመላክቷል።
የልማት አጋሮች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ በአየር ንብረት ፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በተቋማዊ አቅም ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጥሪ ቀርቧል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የጀርመን፣ የጋና የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ቡድን መሪ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም እና የNDCP ከፍተኛ ተወካዮች፤ ኢትዮጵያ ከፖሊሲ ቀረጻ ባለፈ በታዳሽ ኃይል፣ በምግብ ራስን በመቻል እና በአረንጓዴ ከተማ ልማት እያሳየች ያለውን ተግባራዊ እርምጃ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያም “ከአንታሊያ ወደ አዲስ አበባ” በምታደርገው ቀጣይ ጉዞ የአየር ንብረት ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር ለአፍሪካ እና ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተቋቋሚነት ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጧን ከብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
#Ethiopia #COP31 #ClimateAction #GreenLegacy #COP32