ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ እና ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ስትራቴጂካዊ የአጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2019 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ እና ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ስትራቴጂካዊ የአጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።

በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ተቋማዊ ትስስር ለማጠናከር እንዲሁም ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የስምምነቱ አላማ ነው።

ስምምነቱን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እና የዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሚስተር ቭላድሚር ያኩሼቭ፣ በሞስኮ እየተካሄደ ካለው "ለሕዝቦች ነጻነት!" (For the Freedom of Nations!) ንቅናቄ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ፈርመውታል።

የስምምነቱ መፈረም በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል በቆየው ግንኙነት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

ታሪካዊውን የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።

አቶ አደም ፋራህ እና ቭላድሚር ያኩሼቭ ሁለቱ ፓርቲዎች መሠረታዊ የትብብር ስምምነት ከተፈራረሙበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን በመገምገም፣ ለቀጣይ ትብብር ባሉ ዕድሎች ዙሪያ መክረዋል።

ያኩሼቭ በሁለትዮሽ ግንኙነቱ ላይ የታየውን ከፍተኛ መሻሻል በማድነቅ፣ አዲሱ ስምምነት ትብብሩን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

ይህ የትብብር መድረክ ሁለቱም ፓርቲዎች በቅርቡ ያስመዘገቧቸውን የምርጫ ድሎች ተከትሎ መካሄዱ ለተቋማዊ አጋርነታቸው አዲስ መነቃቃትን ፈጥሯል።

ከብልጽግና ፓርቲ አንጻር ስምምነቱ በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ባለው ታሪካዊ መሠረት እና ዘላቂ ወዳጅነት ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ወቅታዊ የጂኦፖለቲካ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማት ጉዳዮች ታሳቢ ያደረገ ነው።

ሁለቱ ሀገራት በተለይም ሉዓላዊነትን፣ ነጻነትን እና የሕዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በማስከበር ረገድ የቆየ የመከባበር እና የአጋርነት ታሪክ አላቸው።

የእ.አ.አ የ1896ቱ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢዎችን ያንበረከከችበት ታሪካዊ ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት የተገነባበት ጠንካራ መነሻም ነው።

ኢትዮጵያ በዚያ ፈታኝ ወቅት ላይ በነበረችበት ጊዜ ሩሲያ ያሳየችው አጋርነትና ድጋፍ፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ምን ያህል ሥር የሰደደና ታሪካዊ መሠረት ያለው መሆኑን ይመሰክራል።

ከዚህም በተጨማሪ ስምምነቱ ብልጽግና ፓርቲ የተለያዩ የጂኦፖለቲካ እና የርዕዮተ ዓለም አመለካከቶች ካላቸው አካላት ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነቱን ለማስፋት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ይህም ተቋማዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር፣ የልማት ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ያስችላል።

በተለይም ለብሔራዊ ሉዓላዊነት መከበር፣ አዳዲስ የቅኝ ግዛት አዝማሚያዎችን ለመመከት፣ ውጤታማ የባለብዙ ወገን ትብብርን (multilateralism) ለማጠናከር እንዲሁም በደቡባዊው የዓለም ክፍል (Global South) ሀገራት መካከል ያለውን አጋርነት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

በመሆኑም ስምምነቱ ከመደበኛ የፓርቲ ግንኙነት ባለፈ፣ የኢትዮጵያና የሩሲያን ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ዘላቂ ትብብር፣ ጠንካራ ተቋማዊ ተሳትፎ እና የጋራ ተጠቃሚነት የሚለውጥ ማዕቀፍ ይፈጥራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም