ወንጪ - ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም፦ የነዋሪዎችን ሕይወት በተጨባጭ የቀየረው የልማት ትሩፋት - ኢዜአ አማርኛ
ወንጪ - ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም፦ የነዋሪዎችን ሕይወት በተጨባጭ የቀየረው የልማት ትሩፋት
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነባው የወንጪ የቱሪዝም ልማት፣ የአካባቢውን መሠረተ ልማቶች በማሟላት የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ከመሠረቱ ከመቀየር ባለፈ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት እንዲመዘገብ እያደረገ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
በተፈጥሮ ጸጋ የታደለችው ነገር ግን በመሠረተ ልማት እጦት ተጋርዳ ለዘመናት በዝምታ ውስጥ የቆየችው ውቧ ወንጪ፣ ዛሬ ገጽታዋ ተቀይሮ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቀልብ የምትገዛ ደማቅ የቱሪዝም ማዕከል ሆናለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ራዕይና ሃሳብ አመንጪነት እውን የሆነው የገበታ ለሀገር የልማት ፕሮጀክት፣ ለወንጪ ተፈጥሯዊ ውበት ዘመናዊ ድምቀትን ከማላበስ ባለፈ የነዋሪዎቿን የዘመናት እንግልት የቀረፈ የታሪክ ምዕራፍ ሆኗል።
ቀደም ሲል የመንገድ፣ የመብራትና የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመሟላቱ የአካባቢው ማህበረሰብ ለእንግልት ተዳርጎ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውሰዋል። ዛሬ ግን ያ ጨለማ ተገፎ በብርሃንና በልማት መተካቱንም ነው የገለጹት፡፡
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚና የአካባቢው ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ወልደጊዮርጊስ፣ ህይወታቸው በባህላዊ እርሻና በከባድ ጉልበት ሥራ ብቻ ተወስኖ ለዓመታት በድካም ማለፉን ያስታውሳሉ።
አሁን ግን በፕሮጀክቱ ትሩፋት አማካኝነት ዘመናዊ መኖሪያ ቤትና የተሻሻሉ የግብርና ግብአቶች ተሟልተውላቸው የኑሮ ዘይቤያቸው ከመሠረቱ መለወጡን ይጠቅሳሉ።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት መንግሥት ዘመናዊ ቤት በመሥራት ብሎም ላም በመግዛት ህይወታቸውን ዳግም እንዳቋቋመላቸው በጥልቅ የደስታ ስሜትና ምስጋና ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ወደ አምቦና ወሊሶ በእግርና በፈረስ ለመጓዝ ቀናት የሚፈጅ አድካሚ ጉዞ ያደርጉ እንደነበር ጠቅሰው፣ ዛሬ በተዘረጋው የአስፋልት መንገድ በቀላሉ ወደሚፈልጉት አካባቢ በምቾት መጓዝ መቻላቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሸለመ አብዲሳ በበኩላቸው፤ የልማት ፕሮጀክቱ ለወንጪ ህዝብ እንደ ሁለተኛ ዕድሜ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ከዚህ ቀደም በማገዶ እንጨት ጭስ እየታፈኑ ምግብ ያበስሉ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ከአስቸጋሪ የኑሮ ዘይቤ ተላቀው፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና በምቹ መኖሪያ ቤት ስልጡን ኑሮ እየመሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የመሠረተ ልማቱ መሟላት አካባቢውን በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በህዝብና በተሽከርካሪ የተሞላ የንግድና የቱሪዝም ማዕከል እንዳደረገው በደስታ ተናግረዋል።
ወንጪ ዓመቱን ሙሉ ለምለም የሆነ፣ ፍል ውሃዎችና የበርካታ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብትሆንም፣ ቀደም ሲል በመሠረተ ልማት እጦት ሳትታወቅ መቆየቷን የአካባቢው ተወላጅና የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ጸጋዬ ተረፋ ያስታውሳል።
አሁን ላይ ግን የመንገድ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎቶች በመሟላታቸው የጀልባ ሽርሽር፣ የፈረስ ግልቢያና ሌሎች የቱሪዝም አገልግሎቶች ተስፋፍተው ለአካባቢው ወጣቶችና ነዋሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጭ መፍጠራቸውን ገልጿል።
ወንጪ ዛሬ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቀልብ እየሳበች መምጣቷን ጠቁሞ፣ የቱሪስት ፍሰቱ ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑንም ተናግሯል።