ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን እውነተኛ የኢኮኖሚ ቁመና የገለጠው አዲሱ GDP ስሌት

የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ጤናማነት እና የእድገት አቅጣጫ የሚመዘነው በተጨባጭ እና ወቅታዊ መረጃ ላይ በተመሠረተ መለኪያ ነው።

ፖሊሲ አውጪዎች ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያሳልፉም ሆነ ባለሀብቶች የገበያውን ስፋት እንዲረዱ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ቆጠራ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይህ መለኪያ ካልተስተካከለ የሀገሪቱን እውነተኛ የኢኮኖሚ ቁመና ማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል።

ኢኮኖሚ በተፈጥሮው ተለዋዋጭ በመሆኑ በየጊዜው አዳዲስ ዘርፎችን እየፈጠረ እና ቅርፁን እየቀየረ ይሄዳል።የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የከተሞች እድገት እና የአገልግሎት ዘርፉ መጠናከር የኢኮኖሚውን መዋቅር በፍጥነት ይለውጣሉ።በዚህ ጊዜ ቀደም ሲል የነበሩ የመለኪያ ዘዴዎች አሁናዊውን እውነታ በሙሉ አቅማቸው ማሳየት ይሳናቸዋል።

በዚህ ምክንያት አገራት የኢኮኖሚያቸውን ትክክለኛ ልክ ለማወቅ የመለኪያ መነሻቸውን በየአምስት እስከ አስር ዓመቱ ማዘመን ዓለም አቀፋዊ አሰራር ሆኗል።አዲስ የኢኮኖሚ ቅርፅን በአሮጌ መለኪያ መመዘን ብዙ የልማት ውጤቶችን ከመዝገብ ውጭ እንዲቀሩ ያደርጋል። ስለሆነም የስሌት ማሻሻያ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አስፈላጊ እርምጃ ነው።

ይህንን ዓለም አቀፋዊ አሰራር በመከተል ኢትዮጵያ የአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) መለኪያዋን በማዘመን ከ2019 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን አዲስ ስሌት በቅርቡ አስተዋውቃለች።በብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀው ይህ ማሻሻያ፣ ለዘጠኝ ዓመታት ሲያገለግል የነበረውን የ2008 ዓ.ም. መነሻ ዓመት ተክቷል።

በዚህ አዲስ ስሌት መሠረት የአገሪቱ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 210 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተረጋግጧል።አዲሱ ስሌት እንደ ዲጂታል ፋይናንስ፣ ካፒታል ገበያ፣ የበጋ መስኖ ልማት እና የኮሪደር ልማት ያሉ ዘመናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ አቅማቸው አካቷል።

በቅርቡ በተካሄዱ የግብርና፣ የኢኮኖሚ ድርጅቶች እና የቤተሰብ ጥናቶች ላይ በመመሥረት መዘጋጀቱ ደግሞ መረጃውን ይበልጥ ተአማኒ ያደርገዋል። በዚህም የሀገሪቱ ትክክለኛ የኢኮኖሚ አቅም ታይቶ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች መካከል አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አረጋግጣለች።

በፖሊሲ ቀረጻ እና በልማት ዕቅድ ዝግጅት ረገድም አዲሱ ስሌት የማይተካ ሚና ይጫወታል። መንግሥት የእያንዳንዱን ዘርፍ ትክክለኛ ድርሻ ሲያውቅ ሀብትን በፍትሐዊነት ለማከፋፈል ይረዳዋል። በተጨማሪም የታክስ አሰባሰብ አቅምን ከሰፊው ኢኮኖሚ አንጻር በመመዘን፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ንግዶችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ለማስገባት ግልጽ መነሻ ይሆናል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ከአበዳሪ ተቋማት እና ከልማት አጋሮች ጋር የምታደርገውን ድርድር አቅም ከፍ ማድረጉ ሌላው ትልቅ አንድምታ ነው።

የአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት መጠን ማደግ የውጭ ብድር ከጂዲፒ ጋር ያለውን ጥምርታ ዝቅ በማድረግ፣ አገሪቱ ለልማት ፕሮጀክቶች የሚሆን ተጨማሪ ፋይናንስ እና የውጭ ኢንቨስትመንት የመሳብ ዕድሏን ያሰፋዋል።በአጠቃላይ ይህ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ ቀጣይ የብልጽግና ጉዞ ትክክለኛ መሠረት የሚጥል ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም