በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የጸደቀው የጋራ መግለጫ በብሪክስ ሀገራት መካከል ያለውን ፍትሃዊነትና አብሮነት የሚያሳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የጸደቀው የጋራ መግለጫ በብሪክስ ሀገራት መካከል ያለውን ፍትሃዊነትና አብሮነት የሚያሳይ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 7/2019(ኢዜአ)፦ በህንድ ኒውደሊ በተደረገው 18ኛው የብሪክስ (BRICS) ጉባኤ የጸደቀው የጋራ መግለጫ በብሪክስ ሀገራት መካከል ያለውን ፍትሃዊነትና አብሮነት የሚያሳይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ የፖሊሲ ልዩ አማካሪ አምባሳደር ምኒልክ አለሙ ገለጹ።
በብሪክስ ጉባኤ ውጤቶች እና ለግሎባል ሳውዝ (Global South) ያላቸው አንድምታ ላይ የሚመክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የምክክር መድረኩን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ከሚገኘው የማሌዢያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን «በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ መጓዝ፤ የብሪክስ ጉባኤ ውጤቶች እና ለግሎባል ሳውዝ ያላቸው አንድምታ» በሚል መሪ ሀሳብ ነው በሸራተን አዲስ ሆቴል የተካሄደው።
በመድረኩ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ የፖሊሲ ልዩ አማካሪ አምባሳደር ምኒልክ አለሙ፤ በህንድ ኒውደሊ በተደረገው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የጸደቀው መግለጫ በብሪክስ ሀገራት መካከል ያለውን ፍትሃዊነትና አብሮነት ያሳያል ብለዋል።
የብሪክስን መንፈስ፣ የጋራ ተስፋ፣ በፍትሃዊነት፣ በዴሞክራሲ፣ በግልጽነት፣ በአካታችነት፣ በትብብር እና በስምምነት ላይ ያለውን ግንዛቤም ያሳያል ነው ያሉት።
የብሪክስ (BRICS) እሴቶች በመግለጫው በስምምነት መጽደቁ ትልቅ ቁርጠኝነትን የሚያሳይ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህም በብሪክስ ሀገራት መካከል ያለውን ፍትሃዊነትና አብሮነት እንዲሁም የብሪክስን ቁርጠኝነት ለማጠናከርና የወደፊት ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን ለመቅረጽ የተደረገ ጥረት እንደሆነ ገልጸዋል።
የጉባኤው መግለጫ የብሪክስ አጋርነትን፣ የንግድ ሥርዓት ማመቻቸትን፣ የንግድ ሰንሰለት አቅርቦትንና የአዲሱን የልማት ባንክ ሚና በማሳደግ የግሎባል ሳውዝ የግብይት ወጪዎችን በመቀነስ፣ የልማት ፋይናንስ ዕድሎችን በማስፋት ከውጭ ምንዛሪ ጫናዎች እፎይታ እንዲያገኙ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሳይበር ደህንነት፣ በዲጂታል ህዝባዊ መሠረተ ልማት እና ወሳኝ በሆኑ ማዕድናት፣ ንጹህ ኢነርጂ ዋጋ ሰንሰለቶች ውስጥ የተደረጉ ትብብሮች ለግሎባል ሳውዝ የሀብት ልማት ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የማሌዢያ ምክትል አምባሳደር ሞህድ አፋንዲ ቢን አቡበከር በበኩላቸው ብሪክስ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች እና በማደግ ላይ ባሉ ኢኮኖሚዎች መካከል ለትብብር አስፈላጊ መድረክ ሆኖ እየወጣ ነው ብለዋል።
የግሎባል ሳውዝ (Global South) ድምጽን ለማጠናከር፣ የበለጠ ሚዛናዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለማስተዋወቅና በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ዓለም አቀፍ ውሳኔዎችን በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና እንዲኖራቸው ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጠናከር፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስፋት፣ የቴክኖሎጂ ትብብርን ለማሻሻል እና በብሪክስ (BRICS) በኩል ዘላቂ ልማት ለማምጣት ሰፊ ዕድሎች እንዳሉም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ ተወካይ ሚስተር ራጂብ ኩማር በህንድ የተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ የጋራ መግለጫ የአባል ሀገራትን ፍላጎት የሚያንጸባርቅና የወደፊት አቅጣጫን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
አባል ሀገራቱ የጋራ ዓላማዎቻቸውን ወደ ተግባራዊ ትብብር እና ተጨባጭ ውጤቶች ለመለወጥ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በዓለም አቀፍ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ጠንካራ ድምፅ እንዲኖራቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ይበልጥ ዴሞክራሲያዊና አካታች እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።