ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራትን እየከናወነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራትን እየከናወነች ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተላላፊ በሽታዎችን ሥርጭት አስቅድሞ በመግታት የላቀ የመከላከል አቅም በመገንባት የጤና ሉዓላዊነቷን እያጎለበተች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ከኅዳር 6 እስከ 8/2019 ዓ.ም ድረስ ባሉት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ዓለም አቀፍ የተላላፊ በሽታዎች መከላከል ሳይንሳዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ለ66ኛ ጊዜ የሚካሄደው ጉባኤው በጤና ሚኒስቴር፣ በአርማወር ሃንሰን ምርምር ኢንስቲትዩትና በአንትወርፕ ትሮፒካል ሜዲሲን ኢንስቲትዩት የጋራ ትብብር የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
ጉባኤው ለተላላፊ በሽታዎች መጨመር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመዳሰስ ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚያመላክቱ ምክረ ሐሳቦች የሚፈልቁበት መሆኑም ተጠቁሟል።
ለዚህም ምርምርን ማዕከል ያደረጉ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እና በዚህ ረገድ ሀገራት ያሉበትን ደረጃ መቃኘትም የጉባኤው ሌላኛው ዓላማ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ውጤታማነት የሚያሳድጉ ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ነው።
የወረርሽኞችን ሥርጭት በመግታትም ኢትዮጵያ ለዓለም የጤና ሥርዓት ውጤታማነት ተምሳሌት የሆነ ትልቅ ስኬት ማምጣቷን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር መቻሏም ለተላላፊ በሽታዎች ሥርጭት መከላከል አቅም መገንባቷን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በርካታ የጤና ኬላዎችን በማቋቋም የጤና ክብካቤን ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
የክትባት ተደራሽነትን ለማስፋት ክትባትን በምርምር የማውጣት ሥራም እንዲሁ ኢትዮጵያ በስፋት እየሰራችበት ያለው ጉዳይ ነው ብለዋል።
የበሽታና ባክቴሪያ ሥርጭት ድንበር ዘለል ነው ያሉት ዶክተር መቅደስ፤ የአፍሪካ ሀገራት በጋራ በመቆም፣ ጥንቃቄን በማጠናከር ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋት ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት።
የሳይንስ ጉባኤውም ሀገራት በቅንጅት እንዲሰሩ፣ ብሎም በጉባኤው የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦችን በጤና ፖሊሲያቸው አካተው እንዲተገብሩ ግብዓት የሚገኝበት መሆኑን አክለዋል።
ኢትዮጵያ ለመድኃኒት አምራቾች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ላይ በመስራት የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር አነሊስ ቨርትሄል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በጤና፣ በምርምርና ዘርፍ ውጤታማ የጤና ሥርዓት በመዘርጋት ምሳሌ የሚሆን ተሞክሮ እንዳላት አንስተዋል።
ኢትዮጵያና ቤልጂየም በተለያዩ መስኮች የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው፤ በጤናው ዘርፍም ሀገራቱ ያላቸው ትብብር እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል።
የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዓለምሰገድ አብዲሳ በበኩላቸው፤ የጤና ሥርዓቱን የሚያጠናክሩ ውጤታማ የምርምር ምክረ ሐሳቦች እየፈለቁ ነው ብለዋል።
መሰል ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ መድረክ በሀገራት መካከል የልምድ ልውውጥን በማሳለጥ በሽታን የመከላከል ዓለም አቀፍ ጥረት እጅግ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።
በጉባኤው ላይ ተመራማሪዎች፣ የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።