የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ለብልሽት እንዳይጋለጥ የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ለብልሽት እንዳይጋለጥ የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ ነው
ጎንደር እና ደሴ ህዳር 7/2019 ዓ/ም የደረሰ ሰብል እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ለጉዳት እንዳይጋለጥ የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የምዕራብ ደምብያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።
የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አላምረው ጥጉ እና ሰለሞን ቦጋለ ፤ በመኸር ወቅት የለማውና የደረሰው ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በመሰብሰብ ከብክነት እየተከላከሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ቀድመው የደረሱትን የገብስ፣ የጤፍና የሌሎች ሰብሎችን ምርት ሰብስበው በማጠናቀቅ፣ ቀሪዎቹን በፍጥነት እየሰበሰቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ ባህላዊና ዘመናዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ምርቱን በደረቅ ቦታ በማከማቸት ያለምንም ብክነት የመሰብሰብ ስራ እየሰሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማናምቶ አገዘው በበኩላቸው፤ በወረዳው በመኸር ወቅት ከ46 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል መልማቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በተደራጀ አግባብ እንዲሰበስብ እየተደረገ ሲሆን፣ እስካሁንም በ36 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
ምርቱ በማከማቸትና በአያያዝ ሂደትም ብልሽት እንዳይገጥመው የተለያዩ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሲሳይ በበኩላቸው፤ የደረሰው ሰብል እየጣለ ባለው ዝናብ ለጉዳት እንዳይጋለጥ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በመኸር ወቅቱ ከለማው 586 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥም ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን በ2018/19 የመኸር ወቅት ከለማው 450 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ በ70 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ የተለያየ ሰብል መሰብሰቡን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ናቸው
አርሶ አደሩ ማሳውን በየቀኑ በማሰስ ቀድሞ የደረሰው ሰብል ለብልሽት እንዳይዳረግ በፍጥነት እንዲሰበሰብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቃሉ ወረዳ የ021 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አደም የሱፍ ፤ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ሰብል በመሰብሰብና ቀሪውንም ፈጥነው ለማንሳት በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመኸሩ ወቅት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት ማሾ፣ ጤፍና ስንዴ ቀድሞ በመድረሱ እየሰበሰቡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የተሁለደሬ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ኢብራሂም አሊ ናቸው።
የሰብል ስብሰባውን በባለሙያዎች ድጋፍና ምክር በመታገዝ ብክነትን በሚቀንስ አግባብ እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።