በአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል የቀረቡ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች የአርሶ አደሩን ምርትና ገቢ እያሳደጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል የቀረቡ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች የአርሶ አደሩን ምርትና ገቢ እያሳደጉ ነው
አርባ ምንጭ፤ ሕዳር 7/2019 (ኢዜአ)--የአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማነትን የሚጨምሩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማላመድና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን አስታወቀ።
የማዕከሉ ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ቱማ አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ በሰብል ዘርፍ 74 የምርምር ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ከአካባቢው የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ ጋር የሚስማሙ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችንና አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።
ማዕከሉ የግብርና ምርምር ሥራዎቹን በጋሞ፣ ኮንሶ፣ ጋርዱላ እና አሌ ዞኖች ሲያከናውን መቆየቱንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በጎፋ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂና ኮሬ ዞኖች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም የተሻሻሉ የአገዳ፣ የብርዕ፣ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን እንዲሁም የእንሰት፣ የሥራስር፣ አትክልትና የፍራፍሬ ሰብሎችን ዝርያ በማሰራጨት ለአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የተሻሻሉና አዳዲስ ዝሪያዎችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን አርሶ አደሩ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ ያሉ ሂደቶችን በተሻለ መንገድ እንዲያከናውን ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ማዕከሉ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በሀገር ደረጃ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረውን ሥራ በማገዝ በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
በማዕከሉ የሰብል ምርምር ሥራ ሂደት አስተባባሪና የዝርያ ማሻሻያ ተመራማሪ ካንኮ ጩንታሌ በበኩላቸው፣ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ፣ በአጭር ጊዜ ለፍሬ የሚበቁና የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን በማፍለቅና በማስፋፋት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በማዕከሉ ለአርሶ አደሩ ከቀረቡ አዳዲስ ዝርያዎች መካከልም "አሸናፊ" የተሰኘው የእርግብ አተር ዝርያ፣ ሁለት የማሽላ እና ሁለት የካሳቫ ዝርያዎችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ከሌሎች የግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በመቀናጀት "ሻፌታ" እና "ሀዋሳ 18" የተሰኙ የስኳር ድንች ዝርያዎችንም በማፍለቅ ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩ መደረጉን ገልጸዋል።
ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በበኩላቸው የማዕከሉ የግብርና ምርምር ውጤቶቹ በተግባር የአርሶ አደሩን ሕይወት እየቀየሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
በጋርዱላ ዞን ደራሼ ወረዳ አርጉባ ጣናኦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዘርፉ ዳትኮ የተሻሻሉ የማሽላ፣ የበቆሎና የቦሎቄ ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ከአካባቢው ማሽላ ከአንድ ሄክታር ከ15 እስከ 20 ኩንታል ሲያገኙ እንደነበረና ከተሻሻለው የማሽላ ዝርያ ከ35 አስከ 40 ኩንታል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በበቆሎም ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር ከ20-30 ኩንታል የሚያመርቱትን የተሻሻለውን መጠቀም ከጀመሩ በኋላ ከ50 ኩንታል በላይ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በማዕከሉ የተሻሻሉት የሰብል ዝርያዎቹ ምርታማነታቸውን በመጨመር ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ ኮዶ አውሳቶ አትሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጋንታ ኡማ በበኩላቸው የተሻሻለ የአኩሪ አተር ዝርያን በማምረት ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"ከአካባቢ አኩሪ አተር ከአንድ ሄክታር 10 ስክ12 ስናገኝ ነበር፤ በማዕከሉ የወጣ የተሻሻለው አኩሪ አተር መጠቀም ከጀመርኩ በኋላ ከሄክታር 35 ኩንታል ማግኘት ችያለሁ" ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር በግብርና ባለሙያዎች ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ የሚደረግላቸው ድጋፍ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዛቸው መሆኑን አስረድተዋል።