ቀጥታ፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ፍራፍሬ በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምረናል - በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን የሎሜ ወረዳ አርሶ አደሮች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2019(ኢዜአ)፦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የአቮካዶ ፍራፍሬ በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን የሎሜ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

ሁሉንም ዓይነት ፍራፍሬ በማምረት የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያሻሽል የገቢ አቅም እየገነቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር በጅማ ከተማ የሚከበረውን 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማስመልከት የኦሮሚያ ክልልን ጸጋዎች የሚያስተዋውቅ የመገናኛ ብዙሃን የመስክ ጉብኝት ቀጥሎ እያካሄደ ነው።

የመደመር መንግሥት በዝናብ ጥገኝነት ተንጠልጥሎ የቆየውን የኢትዮጵያ ኋላቀር የግብርና ልማት ባህል በመቀየር የገጠር መዋቅራዊ ሽግግርን የሚያፋጥን የምርታማነት አቅም እየገነባ ይገኛል።

የግብርና ምርታማነት ማሻሻያ የልማት ኢኒሼቲቮችም በከተማ ግብርና፣ በመስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ክላስተር የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ አስቻይ ምኅዳር ፈጥሯል።

የመደመር ፍልስፍና ሀገር በቀል እውቀትና ሀብትን ጥቅም ላይ በማዋል የማኅበረሰቡን የሥራ ባህል በመቀየር የተረጅነትን አስተሳሰብ በማጥፋት ትርፍ አምራች አርሶ አደሮችን መፍጠር አስችሏል።

በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ሎሜ ወረዳ በፍራፍሬ ልማት የተሰማሩት አርሶ አደር ቱፋ ዓለሙ እንዳሉት፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኢኒሼቲቭ ከአርሶ አደርነት ወደ ኢንቨስተርነት የሚቀይር ዘርፍ ነው።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በ2010 ዓ.ም በሰጣቸው ምክረ ሐሳብ መሠረት ከሦስት ዓመት በኋላ ውጤቱን በተግባር አይተናል ብለዋል።

በዚህም ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሎሚ፣ ቃሪያና ፖፖያን ጨምሮ ከአሥር ዓይነት በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የሆነውን ሐስ የተሰኘ የአቮካዶ ፍራፍሬ ዝርያ በማምረትም በአምስት ዙር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ጀምሬያለሁ ብለዋል።

የተፈጠረላቸው የገበያ ትስስርም አሁን ላይ ስፔንን ጨምሮ ለአውሮፓና ለዓለም ገበያ ምርታቸውን እያቀረቡ መሆናቸውን አንስተዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር ሰለሞን ታደሰ በበኩላቸው፤ የዓሳ፣ የማንጎና ሌሎች የፍራፍሬና የግብርና ልማት ዘርፎች የምርታማነት አቅማቸውን በማጎልበት በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ መሻሻል ማምጣቱን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር በሁለት ሔክታር መሬት ላይ የሚያለሙት ሐስ የተሰኘ የአቮካዶ ዝርያም ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሻሻል እንደጀመሩ ተናግረዋል።

የግብርና ሙያተኞች የሚያደርጉላቸው ድጋፍና ክትትልም ከፍተኛ ትዕግስት የሚጠይቀውን የፍራፍሬ ልማት ለውጤት እያበቃቸው እንደሚገኝ አንስተዋል።

በቀጣይም ከራሳቸው አልፎ የኢትዮጵያን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በዓለም ገበያ በማቅረብ የሀገራቸውን ስም ለማስጠራት ከፍተኛ ርዕይ እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን የቦራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ሙስባህ ሙስጠፋ እንዳሉት፤ አርሶ አደሮች በዓሳ፣ በዶሮና በፍራፍሬ ልማት በክላስተር በመደራጀት ውጤታማ የምርታማነት አቅም እየፈጠሩ ነው።

በሎሜ ወረዳ 54 አርሶ አደሮች በማኅበር ተደራጅተው አቮካዶን በክላስተር በማልማት ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የአርሶ አደሮች ውጤታማ መሆን ሌሎች የወረዳው ነዋሪዎችን በማነቃቃት ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም