COP32 የኢትዮጵያን የአየር ንብረት አጀንዳ ለማራመድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
COP32 የኢትዮጵያን የአየር ንብረት አጀንዳ ለማራመድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2019 (ኢዜአ)፦ COP32 የኢትዮጵያን የአየር ንብረት አጀንዳ ለማራመድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የCOP32 ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴን በመሰብሰብ አጠቃላይ የሥራ ሂደቱን ዛሬ ጠዋት መገምገሙን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝግጅቶችን ከፈተሹ በኋላም ሥራዎች የሚመሩበት ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ መስጠታቸውን አመልክተዋል።
ጉባኤውን በስኬት ለማስተናገድ ሁሉም ግብረ-ኃይሎች ተናብበው እንዲሠሩ በማድረግ፣ የተቀናጀ ሁሉን አቀፍ የመንግሥት አካሄድ መከተል ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት አሳስበዋል።
COP32 ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከመሆኑ ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት እና የአካባቢ ጥበቃ አጀንዳን ለማራመድ፣ አጋርነትን ለማጠናከር፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲሁም ብሔራዊ ጥረቶቻችንን ወደ ዘላቂ ውጤት ለመለወጥ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።