ቀጥታ፡

የባሕር በር ለኢትዮጵያ የህልውና፣ የልማትና የደኅንነት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2019 (ኢዜአ)፦የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የህልውና እና የደኅንነት ጉዳይ መሆኑን የናይልና የቀይ ባሕር ስትራቴጂክ ፎረም ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ተፈራ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የናይልና የቀይ ባሕር ስትራቴጂክ ፎረም ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ተፈራ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የህልውና እና የደኅንነት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተለዋዋጭነት ውስጥ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ማግኘት እጅግ አሳሳቢና አንገብጋቢ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የዜጎችን ህልውና፣ ሰላም እና ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል እንጂ የቅንጦት ጥያቄ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የቀይ ባሕር አካባቢ ከዓለም አቀፍ የንግድ መተላለፊያነቱ ባለፈ አደገኛ የፀጥታና የጂኦ-ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መግባቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከሌለ የቀይ ባሕር ደኅንነት ሊረጋገጥ እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተዋል።

በቀደሙት ጊዜያት ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን እንደምትፈልገው ሁሉ በአሁኑ ወቅትም ቀይ ባሕር ራሱ ለደኅንነቱ ሲል ኢትዮጵያን የሚፈልግበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት ሂደት በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በታሪክም ሆነ በጂኦግራፊ ተቀባይነት ያለው ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ይህንን ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ሕጋዊ እውነታ በጥልቀት በመመርመር ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ ማሳወቅ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም