ቀጥታ፡

አዲስ አበባ፡ስምና ግብር የታረቁባት የአፍሪካ መዲና

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ከ140 ዓመታት በኋላ አቧራዋን አራግፋ እንደ ስሟ የፈካችው አዲስ አበባ

የአዲስ አበባ ከተማ የቀድሞ ገጽታ ስሟ ከግብሯ የቀደመበት፣ ተግባርና ሥራ ያልተባበሩበት ነበር። አንዲት ከተማ ስሟን ለመምሰል ስንት ዘመን ይፈጅባት ይሆን? አዲስ አበባ ከተመሠረተች 140 ዓመት ብታስቆጥርም አበባነቷ በገጽታዋ መታየት የጀመረው ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነው። በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳርቻ ልማት እንደ ስሟ አብባና ፈክታ እየተስተዋለች ነው። ከተማዋ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን በማከናወን ስሉጥ ከተማነቷን የበለጠ እያስመሰከረች፤ ዲጂታል መሠረተ ልማት በማስፋት ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎቿ ምቹ መሆኗን እያረጋገጠች ትገኛለች። ዜጎች ካልተመቸና ከተጨናነቀ አኗኗር ተላቀው በምቹ የመኖሪያ አካባቢ እንዲኖሩ በማድረግ ጤናማነታቸው እየተጠበቀና ምርታማነታቸው እያደገ ይገኛል።

አቧራዋን ያራገፈችበት ዘመን

የመደመር መንግሥት ለከተማዋ የሰጠው ትኩረት ገጽታዋን ቀየረ። ሁለት ትላልቅ ሥራዎች ለውጡን መሩት፤ እነርሱም የወንዝ ዳርቻ ልማትና የኮሪደር ልማት ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማት ከተማንና ገጠርን እኩል እየቀየረ ያለና የከተሞችን ገመና የገለጠ ነው።

እርሳቸው እንደተናገሩት ከተሞች ከዚህ ቀደም ሕይወት በሰቆቃ የሚገፋባቸው የመከራ ዳሶች፣ ንግድና አገልግሎት የማይሳለጥባቸው መተራመሻዎች ነበሩ። ፋይናንስ፣ ትራንስፖርት፣ መዝናኛና ታሪክ የማይተሳሰሩባቸው መንደሮችም ነበሩ። በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማቶች ከተሞች የዘመናዊ ከተማ መልክ መያዝ በመጀመራቸው ለመኖሪያ የተመቹ፣ ለንግድና ለኮንፈረንስ የተስማሙ፣ ቢያስጎበኟቸው የማያሳፍሩና ተምሳሌት ተደርገው የሚጠቀሱ እየሆኑ መጥተዋል። ዛሬ ኢትዮጵያ ''የአፍሪካ ውብ አበባ'' ተብላ ብትጠራ እውነታ እንጂ ባዶ ሙገሳ ተደርጎ አይወሰድም።

የአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ በውጭ ዜጎች እንዴት ይገለጻል?

የአዲስ አበባ ከተማ ለውጥ ለዓይን የሚሞላ በመሆኑ የከተማዋን ጽዳት፣ ውበትና ፍካት የተመለከተ ሁሉ የሚመሰክረው ሀቅ ሆኗል። ለረጅም ዓመታት በከተማዋ የኖሩት የሩሲያው አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴሬኪን ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መናገሻ ብትሆንም የከተማነት ገጽታ ግን ከአሁኑ ጋር የተቃረነ እንደነበር ያነሳሉ። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተማዋ የተመዘገበው ለውጥ ግን የከተማዋን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት በተግባር የገለጠ መሆኑን አረጋግጠዋል። የከተማዋን ለውጥ ለከተማዋ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ለእነሱም የኩራት ምንጭ ነው ብለዋል።

የኢንዶኔዥያው የቀድሞ አምባሳደር አል ቡስራ ባስኑር በበኩላቸው ስለአዲስ አበባ ለውጥ እማኝነታቸውን የገለጹት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የነበረው የከተማዋ ገጽታና አሁን የታየው ለውጥ የማይታመን ሲሉ ነው። የአዲስ አበባ የአሁን መልክ ማሳያ ሰፋፊና ምቹ መንገዶች ጽዱና ውብ ከተማ አድርገዋታል።

የአዲስ አበባ ውበት ፈክቶና ደምቆ አሁን ላይ ከተማዋን ከኒው ዮርክና ከጄኔቫ ጋር ማወዳደር የሚያስችል ቁመና ላይ ትገኛለች ሲሉ የተናገሩት የዴንማርኩ አምባሳደር ሱነ ክሮግስትሩፕ ናቸው። የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ በኮሪደር ልማት ከተማዋ ሰፋፊ መንገዶች፣ ምቹ የእግረኛ መንገዶችና መናፈሻዎች ያሏት ዘመናዊ ከተማ መሆኗን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ከተማዋን ሊጎበኙና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን ሊታደሙ የመጡ የውጭ ሀገር ዜጎችም የአዲስ አበባን ውበትና ለውጥ እጅን በአፍ የሚያስጭን ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆን አርአያ ተግባር መሆኑን በተደጋጋሚ ያስረዳሉ።

የከተማዋ ውብ መልክ የመጽሐፍ ምስክርነትና የዓለም እውቅና

የአዲስ አበባ ከተማ የትናንትና የዛሬ ንጽጽር በመጽሐፍም ተመዝግቧል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በግንቦት 2018 ዓ.ም., በአራት ደራሲያንና ዓለም አቀፍ ምሁራን ተጽፎ የተመረቀው ''The Remaking of Addis Ababa: Transformation from 2020–2025'' የተሰኘው መጽሐፍም አዲስ አበባ ከ2012 እስከ 2017 ዓ.ም. (2020–2025) ባሉት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበችውን ፈጣን የከተማ ልማት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታና የአረንጓዴ ሽግግር ዳሷል።

መጽሐፉ ቀደም ሲል የተጎሳቁሉትና ንጽህና ያልነበራቸው አካባቢዎች ዛሬ እንዴት በዘመናዊ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ በሰፋፊ መንገዶችና በአረንጓዴ መናፈሻዎች እንደተተኩ በመረጃ አስደግፎ ያሳያል። መጽሐፉ ከተማዋ ከማይመች አኗኗር ተላቃ ለአየር ንብረት የማይበገር፣ ጽዱና ዘመናዊ የ''ስማርት ሲቲ'' ገጽታን እንዴት እንደተላበሰችም ይዳስሰል።

የአዲስ አበባ ከተማዋ ገጽታ የምሁራን ምስክርነት ያገኘ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማቶችንንም የተቸረው ነው። አዲስ አበባ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በአረንጓዴ ስፍራዎችና በዘመናዊ የሕዝብ ትራንስፖርት ባመጣችው ሰው ተኮር ለውጥ በጥቅምት 2019 ዓ.ም. (ኦክቶበር 2026) በUN-Habitat እና በቻይና መንግሥት የሚዘጋጀውን የ2026 የሻንሃይ ዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት ሽልማት ከ92 ተወዳዳሪ ከተሞች ልቃ አሸንፋለች። ከዚህም በተጨማሪ በ2026 የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም አቅሟ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፣ ቀደም ሲልም የሴኡል ስማርት ሲቲ ሽልማትን በማግኘት ስኬቷን በዓለም አቀፍ መድረክ አስመስክራለች።

የአፍሪካ አዲሲቷ አበባ

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መናገሻ ከተማ እንደመሆኗ ከዚህ ቀደም የአህጉሪቷን ስብሰባዎች ስታስተናግድ ኖራለች። አሁን ግን ለውጧ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን አጉልቶ በርካታ ጉባዔዎችን እንድታስተናግድ አስችሏታል።

የከተማዋ ለውጥ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከልነቷን በማሳደጉ በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከተማዋ ከ200 በላይ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን አስተናግዳለች።

ከአምስት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያሏት፣ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 355 ሜትር ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ አሁን ከስሟ ጋር እየተገናኘች ነው። ከ140 ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ተብላ ስትሰየም የተመኘችው ውበት ዛሬ በተግባር ተገልጧል። ከተማዋ አቧራዋን አራግፋ፣ በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት ታድሳ ስሟንና ግብሯን አስታርቃለች። ትናንት በመንገደኞች ዓይን ይታይ የነበረው የከተማዋ ድካም ተረስቶ፣ ዛሬ የዓለም መሪዎች የሚያደንቋትና መጻሕፍት የሚመሰክሩላት የአፍሪካ ኩራት ሆናለች።

አዲስ አበባ ዛሬ ስሟን የመሰለች፣ ለነዋሪዎቿ የምትመችና ለመጪው ትውልድ የምትተርፍ እውነተኛ የአፍሪካ አበባ ሆና ፈክታለች። ታሪክ በመጻሕፍት፣ ዓለም በሽልማት፣ ዲፕሎማቶችም በአድናቆት የመሰከሩለት የአዲስ አበባ ዳግም ልደት ዛሬ በገሃድ እየታየ ነው። ለዘመናት ''ስንት ዓመት ይፈጅባት ይሆን?'' ብለን የጠየቅንላት ከተማ ዛሬ መልሱን በተግባር ሰጥታናለች። አዲስ አበባ ዛሬ እንደ ስሟ አዲስና ውብ አበባ ሆናለች።

አዲስ አበባ ለአፍሪካና ለዓለም ውብ መሆኗን በተግባር ገልጣለች፤ ራሷን በገጸ በረከትነት ሞሽራለች። ዓለም ዓይኖቹን እርሷ ላይ በመጣል ታላላቅ ጉባዔዎችን ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል፤ አሁንም እያደረገ ነው። አዲስ አበባም በደስታ እጇን ዘርግታ እንግዶቿን ትቀበላለች። ስምና ግብሯ ተጣጥመው ዘመናትን ይሻገራሉና።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም