የዓድዋ ድል የሉዓላዊነትና የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አቅም ሕያው ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የሉዓላዊነትና የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አቅም ሕያው ማሳያ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2019 (ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል የሉዓላዊነትና የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አቅም ሕያው ማሳያ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የቀጣናው የአስተዳደርና የሕግ የበላይነት አማካሪ ዴቪድ ኦሞዙዋፎህ ገለጹ።
የዓድዋ ድል ሕዝቦች በቁርጠኝነታቸውና በጋራ ጥንካሬያቸው የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ መቅረጽ እንደሚችሉና ፈተናዎችን የማለፍ አቅም እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነውም ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የቀጣናው የአስተዳደርና የሕግ የበላይነት አማካሪ ዴቪድ ኦሞዙዋፎህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዓድዋ ድል ሉዓላዊነቱን ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ ለመስጠት ያልተንበረከከ ሕዝብ ፅናትና ቁርጠኝነት ማሳያ ነው።
ይህ ታሪካዊ ድል ከወታደራዊ ድልነቱ ባለፈ፣ በዘመናዊው ዓለም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች የውጭ ጫናዎች ለሚገጥሟቸው ማኅበረሰቦች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።
የዓድዋ ታሪክ የፅናት ታሪክ ነው፤ የራሳችን ባለቤት እኛው ነን፣ ከውጭ ለሚመጣ ጫናም አንበረከክም ያለ ሕዝብ ታሪክ ነው በማለት አብራርተዋል።
የዓድዋ ድል መልዕክት ሕዝቦች በቁርጠኝነታቸው፣ በጋራ ጥንካሬያቸው እና በፅናታቸው የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ የመቅረጽና ፈተናዎችን የማለፍ አቅም እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነው።
ሀገራትና ማኅበረሰቦች የተለያዩ ጫናዎችን በሚጋፈጡበት በአሁኑ ወቅትም ዘላቂ ነፃነትና ዕድገት በውጭ አካላት ላይ ሊመሠረት እንደማይችል አንስተዋል።
ስለሆነም ራስን መቻል መሠረታዊ መርህ ሆኖ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከውጭ የሚመጣ ማንም አዳኝ የለም፤ የራሳችሁ አዳኞች እናንተው ራሳችሁ ናችሁ ያሉት አማካሪው፤ ይህም የራስን ዕድል በራስ የመወሰንን አስፈላጊነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የ1888 ዓ.ም ታሪካዊው የዓድዋ ድል በአፍሪካ ፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ ከመሆኑ ባሻገር፣ የጋራ አንድነትና ጀግንነት ተምሳሌት መሆኑንም ተናግረዋል።
የድሉ መንፈስም አፍሪካ ለኢኮኖሚ ነፃነት፣ ለቀጣናዊ ትስስር እና ለዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለምታደርገው ወቅታዊ ሽግግር ዘላቂ መመሪያና የመነሳሳት ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን አማካሪው ገልጸዋል።