ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር ልማት ዘመናዊ የአኗኗር ሥርዓት እንድንከተል አስችሎናል - በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን አደአ ወረዳ አርሶ አደሮች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ)፦ የገጠር ኮሪደር ልማት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በማሻሻል ዘመናዊ የአኗኗር ሥርዓት እንዲከተሉ እያደረጋቸው መሆኑን በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን አደአ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር በጅማ ከተማ የሚከበረውን 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማስመልከት የመገናኛ ብዙኃን የመስክ ጉብኝት እያካሄደ ነው።

በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ጸጋዎችን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው ጉብኝት በመደመር እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን መመልከት ተችሏል።

በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን አደአ ወረዳ የገጠር ኮሪደር ልማት እንቅስቃሴም ከተጎበኙ መካከል ይገኝበታል።

መንግሥት የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የገጠር ኮሪደር ልማት መርሐ ግብር ሥራ ላይ በማዋል የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት በተጨባጭ እየቀየረ ነው።

አርሶ አደር ሲሳይ ግርማ፤ የኮሪደር ልማቱ ወደ አካባቢው ከመምጣቱ በፊት ከእንስሳት ጋር አንድ ላይ ይኖሩ እንደነበርና በዚህም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ አስታውሰዋል።

በመንግሥት ድጋፍና በባለሙያ እገዛ በአካባቢው የተከናወነው የገጠር ኮሪደር ልማት የመንገድ፣ የውኃና ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት እንዲሟላ በማድረግ ዘመናዊ የአኗኗር ሥርዓት አስገኝቶልናል ብለዋል።

ከመሠረተ ልማት ዝርጋታው ጎን ለጎንም በመንግሥት የተሰጣቸው ሥልጠናም የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንዳሻሻለላቸው ገልጸዋል።

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ አዲስ አካሉ በበኩላቸው፤ የገጠር ኮሪደር ልማቱ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት ባለቤት አድርጎናል ብለዋል።

ግንባታው የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ እንዲያገኙ በማስቻል ትልቅ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እፎይታን እንደቸራቸው ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ ጥሩ ነገር ይዞ መምጣቱን ገልጸው፤ መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነትም ያሳየበት መሆኑን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም