ኢትዮጵያ ለመድኃኒት አምራቾች አስቻይ የፖሊሲና የኢንቨስትመንት ምኅዳር ፈጥራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለመድኃኒት አምራቾች አስቻይ የፖሊሲና የኢንቨስትመንት ምኅዳር ፈጥራለች
አዲስ አበባ፤ህዳር 6/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለመድኃኒት አምራቾች አስቻይ የፖሊሲና የኢንቨስትመንት ምኅዳር መፍጠሯን የኢትዮጵያ የመድኃኒት እና ሕክምና መገልገያ አምራች ዘርፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
የመደመር መንግሥት የወሰደው የፖሊሲ እርምጃና የሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለአምራች ዘርፉ ምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በዚህም በኢትዮጵያ በተለያዩ አምራች ዘርፎች ለሚሰማሩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አልሚዎች አስቻይ ምኅዳር በመፍጠር በፍጥነት ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ልዩ ልዩ የፖሊሲ ማበረታቻዎች ተዘርግተዋል።
በተለይም የአምራች ዘርፉን ማንሰራራት ለማላቅ ተግባራዊ የተደረገው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያየ ምክንያት ማምረት ያቆሙና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ አስችሏል።
የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችም የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት የመሸፈን አቅም እያጎለበቱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ የመድኃኒትና ሕክምና መገልገያ አምራች ዘርፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመድኃኒት ፍላጎትን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል ምኅዳር ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ የመድኃኒት አምራቾችን ለማበረታታት የወሰደችው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማሻሻያም ከአፍሪካ ቀዳሚ እንዳደረጋት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርታማነት አቅም አህጉራዊ ቀዳሚነትም 70 በመቶ የሚሆነውን ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት በሚሸፍኑ 14 ሀገሮች በተደረገ ጥናት እንደተረጋገጠ ጠቁመዋል።
የታክስ ማበረታቻ፣ የገበያ ሥርዓት፣ የተሻለ የምርት ዋጋ አቅርቦት፣ ጠንካራ የቁጥጥር ተቋም፣ ምቹ የጉምሩክ ሥርዓትና ለግዥ በሚሰጡ ቅድመ ክፍያዎች የቀዳሚነቷ ማረጋገጫ ናቸው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ለሀገር ውስጥ አምራቾች የአምስት ዓመት የማዕቀፍ ኮንትራት የሚፈጥር ሀገር እንደሌለ ገልጸው፤ ይህም ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት እና የፖሊሲ አቅጣጫ ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ በሀገር በቀል የመድኃኒት ምርት ራስን የመቻል ጉዞ ከፍተኛ እመርታ ማሳየቱን ጠቁመው፤ ባለፉት አራት ዓመታት ከነበረበት ስምንት በመቶ ወደ 44 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል።
አሁን ላይ አምራች ዘርፉ በሙሉ አቅም እንዲሰራ የፋይናንስ አቅርቦት ላይ እየተደረገ ያለው ጥረት መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ምርቷን ማቅረብ የምትችልበት እምቅ አቅም መኖሩን ጠቁመዋል።
በቀጣናው ያለውን ገበያ መቆጣጠር የጤና ሥርዓቱን ብቻ ሳይሆን የሀገርን ሉዓላዊነት የመደገፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።