ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ68 ሺህ በላይ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ

አዲስ አበባ፤ህዳር 6/2019(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ68 ሺህ በላይ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ አስታወቁ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ኃላፊው፣ በአዲስ አበባ በ2019 በጀት ዓመት ወደ 375 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል።

በዚህም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለ70 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተያዘው ዕቅድ መሰረት የዕቅዱን 98 በመቶ በማሳካት ከ68 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብዝኅ ኢኮኖሚ አቅጣጫም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና በዲጂታል የልማት ዘርፎች ለመዲናዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራም ቱሪዝምና አገልግሎት፣ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ ከተማ ግብርና፣ ኮንስትራክሽንና ሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን አንስተዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማትም የሥራና ሠራተኛ ገበያውን በማሳለጥ ወጣቶች በራሳቸው ተደራጅተው ጭምር ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የሚችሉበትን ወሳኝ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም ወጣቶች ዕውቀትና ክህሎታቸውን በመጠቀም በሀገር ውስጥና በውጭ የሥራ ገበያዎች ተወዳዳሪና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል በመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ የተሰናሰለ የልማት ሥራም የዜጎችን ሁለንተናዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማስፋት ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አንስተዋል።

ቢሮውም የያዛቸውን ዕቅዶች በላቀ ደረጃ በማሳካት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከወትሮው በተለየ ዝግጁነት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም የከተማዋን የልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የወጣቶች የክህሎትና የቴክኒክ ሥልጠናዎችን በማስፋት ለገበያ ተኮር የክህሎት ልማት ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

የክህሎትና የቴክኒክ ሥልጠና የወሰዱ ዜጎችን በተዋረድ በተፈጠረው አደረጃጀት መሰረት የፋይናንስ ብድር፣ የመስሪያ ቦታና ተያያዥ ድጋፎችን በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም