በደቡብ ምእራብ ኦሮሚያ ዞን በሩብ በጀት አመቱ ከጎብኚዎች ከ250 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምእራብ ኦሮሚያ ዞን በሩብ በጀት አመቱ ከጎብኚዎች ከ250 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኘ
መቱ፤ ህዳር 6/2019 (ኢዜአ):- በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከሀገር ውስጥና ከውጭ አገር ጎብኚዎች ከ250 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የዞኑ ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በተፈጥሮ ሀብት፣ በታሪካዊ ቅርሶችና በባህላዊ እሴቶች የታደለ አካባቢ በመሆኑ ለቱሪዝም ልማት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል።
በቅርብ ዓመታት በመንግሥትና በአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎችና የመስህብ ስፍራዎችን የማልማት ሥራዎች ወደ ዞኑ የሚጎርፉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርገዋል።
የቱሪዝም ዘርፉን ለአካባቢው ኢኮኖሚ ዕድገትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ቁልፍ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም እየተደረገ ያለው ጥረትም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲመጣ አስችሏል።
የዞኑ ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ደበላ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፣ በበጀት ዓመቱ በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመንከባከብና በማስተዋወቅ ከዘርፉ አንድ ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።
ለእቅዱ ስኬትም ለቱሪስት መስሕቦቹና መዳረሻዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዞኑ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት፣ የጉማሮ ሻይ ተክል፣ ያዮ ተፈጥሮ ደን፣ የጉራቻ ዋሻዎች ይገኙባቸዋል።
እንዲሁም ጥንታዊቷ ጎሬ ከተማን ጨምሮ ሶር ፏፏቴ፣ ዳንጋዋጅ ፏፏቴ እና ኢሊኬና ፏፏቴ በዞኑ ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ጥቂቶቹ መሆናቸውን እስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሶስት ወራት እነዚህን የቱሪዝም መዳረሻዎች ከጎበኙ 100 ሺህ የሀገር ውስጥ እና ከውጭ ጎብኚዎች 250 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የቱሪስት ፍሰት መጨመሩን ተከትሎ ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያደገ መምጣቱንም አክለዋል።
እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ከ400 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥና ከአራት ሺህ የሚበልጡ የውጭ ጎብኚዎች ዞኑን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ወንድሙ አስታውቀዋል።
በዞኑ የሚገኙ መስህቦችን በአግባቡ በማልማትና የመጎብኘት እድላቸውን በማሳደግ ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራ ምቹ መደላድል እንዲፈጥርም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህ ረገድ በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን የመንከባከብና የማስተዋወቅ ስራዎች በትኩረት በመሰራታቸው በዘርፉ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አውሰተዋል።
በአካባቢው በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መኖራቸውን የገለፁት ምክትል ሃላፊው፣ በዘርፉ እየተመዘገበ የሚገኘውን ኢኮኖሚ ይበልጥ ለማሳለጥ ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሰራም አስረድተዋል።