የአየር ንብረት ቅድሚያ ጉዳዮችን ከብሔራዊ በጀትና ኢንቨስትመንት ጋር ማቀናጀት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ቅድሚያ ጉዳዮችን ከብሔራዊ በጀትና ኢንቨስትመንት ጋር ማቀናጀት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ቁርጠኝነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር የፋይናንስ ሚኒስቴሮች የአየር ንብረት ቅድሚያ ጉዳዮችን ከብሔራዊ በጀትና ኢንቨስትመንት ጋር ማቀናጀት እንዳለባቸው የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
31ኛው የተባበሩት መንግስት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) እየተካሄደ ይገኛል።
የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን በተዘጋጀ ከፍተኛ ደረጃ የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።
ሚኒስትሯ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማካፈል፣ የአየር ንብረት ጥበቃ ርምጃዎችን ከብሔራዊ የልማት አጀንዳ፣ ከኢንቨስትመንት እና ከኢኮኖሚያዊ የመቋቋም አቅም ጋር በተቀናጀ መንገድ የማስፈጸምን አስፈላጊነትን አንስተዋል።
አክለውም፣ የአየር ንብረት ጥበቃ ቁርጠኝነቶችን ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመቀየር የፋይናንስ ሚኒስቴሮች የአየር ንብረት ቅድሚያ ጉዳዮችን ከብሔራዊ በጀት፣ ከመንግሥት ኢንቨስትመንት እና ከፋይናንስ ስትራቴጂዎች ጋር በማቀናጀት የሚኖራቸውን ወሳኝ ሚና አጉልተው ገልጸዋል።
በተጨማሪም፣ ከተቀመጡ ግቦችና ዕቅዶች ወደ ተጨባጭ ኢንቨስትመንትና የልማት ውጤቶች ለመሸጋገር፣ ፖሊሲዎችን፣ ተቋማዊ አቅምን፣ የፋይናንስ ሀብቶችን እና የትብብር አጋርነቶችን በተቀናጀ መንገድ ማስኬድ ያለውን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።