ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ዩኤን ወመን በፍትሃዊ የአየር ንብረት ምላሽ አሰጣጥ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት የስርዓተ ጾታ እኩልነትና የሴቶችን አቅም ማጎልበቻ ድርጅት ( ዩኤን ውመን) ሁሉን ያሳተፈና ፍትሃዊ የአየር ንብረት ምላሽ ለማስፈን የጋራ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ አስታወቁ።

31ኛው የተባበሩት መንግስት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) እየተካሄደ ይገኛል።

የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን፣ ከተባበሩት መንግሥታት የስርዓተ ጾታ እኩልነትና የሴቶችን አቅም ማጎልበቻ ድርጅት ( ዩኤን ውመን) የፖሊሲ፣ የፕሮግራምና የመንግሥታት መካከል ግንኙነት ዳይሬክተር ከሆኑት ሳራ ሄንድሪክስ ጋር ተወያይተዋል።

የሁለቱ ወገኖች ውይይት በፆታ እኩልነት፣ በመንግሥት ፋይናንስ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሚደረጉ እርምጃዎች መካከል ባለው ትስስር ላይ ያተኮረ ነው።

በውይይቱ ወቅት ዳይሬክተሯ ሳራ ሄንድሪክስ፣ ኢትዮጵያ የፆታ እኩልነት ጉዳዮችን በመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ውስጥ በማካተት ረገድ እያሳየች ያለውን ተጨባጭ እድገት አድንቀዋል።

በተለይም የበጀት ድልድልን ከፆታ እኩልነት አንፃር የመለየትና የመከታተል ሥርዓትን (Gender Budget Tagging) በመተግበር ሀገሪቱ ያስመዘገበችውን ውጤት በአድናቆት አንስተዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ አካላት፣ የአየር ንብረት ፋይናንስ ለፆታ እኩልነት ተገቢውን ትኩረት የሚሰጥ እንዲሁም ሁሉንም ያሳተፈ፣ ፍትሃዊና እኩልነትን የሚያረጋግጥ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለማስፈን በሚያበረክተው ሚና ላይ በስፋት ተወያይተዋል።

ሁለቱም ወገኖች ለፆታ እኩልነት ተገቢውን ትኩረት የሚሰጥ የአየር ንብረት ፋይናንስን ለማሳደግ በትብብር መሥራታቸውን ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም