ቀጥታ፡

የቅዳሜና እሁድ ገበያ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል -የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች

ጅግጅጋ ፣ህዳር 5/2019(ኢዜአ)፦ የቅዳሜና እሁድ ገበያ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በቀላሉ እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ የጅግጅጋ ከተማ  ነዋሪዎች ገለጹ።

በጅግጅጋ ከተማ የቅዳሜና የእሁድ ገበያ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በአንድ ስፍራ በማቅረብ ለነዋሪዎች የተመቻቸ ግብይት እየፈጠረ ይገኛል።

በከተማው የቆርዴሬ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትዝታ ሀይሉ የቅዳሜና እሁድ ገበያ የግብርና ምርቶች በአንድ ማዕከል በማቅረብ ሸማቹ በቂ ምርት በአይነት እንዲያገኝ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም የሸማቹን ጉልበት፣ ጊዜና ወጪ መቆጠቡን አመልክተዋል። ወይዘሮ ሁኩን አብዲ በበኩላቸው የቅዳሜና እሁድ ገበያ ምርቶችን በአንድ ማዕከል፣ በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ በማድረግ ገበያን እያረጋጋ ነው ብለዋል።

ምርቶችን ከአምራቾች ተረክበው በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከከተማዋ ነጋዴች መካከል አቶ ጌታቸው ነጋ ናቸው ። መንግሥት አምራቾችን ከነጋዴዎች ጋር በማስተሳሰር ሸማቾች ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። ወይዘሮ አነብ አረብ በበኩላቸው ከአምራቾች ምርት ተረክበው ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት በቂ ምርት መኖሩን አመልክተዋል።

የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የቆር ዴሬ ክፍለ ከተማ የንግድ ሥራ አስክያጅ አቶ አብዱላሂ ሁድሌ የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች ሸማቾች የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እያስቻሉ መሆኑን ተናግረዋል። በክፍለ ከተማው የምርት አቅርቦት ለመጨመርና የገበያ ትስስር ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል። በጅግጅጋ ከተማ አምስት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መኖራቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም