ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የምትመሰል ሀገር ሆናለች- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የምትመሰል ሀገር ሆናለች- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የምትመሰል ሀገር መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጀመርናቸው ሥራዎች የአካባቢ ጥበቃ፣ የዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የደህንነትና የብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ ቁልፍ ስልቶችም ናቸው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማፋጠን ለትውልድ ተሻጋሪ ብልጽግናን የማረጋገጥ ብሔራዊ ንቅናቄ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ይህንኑ ተግባራዊ ተሞክሮ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ በማስፋት በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን ተፅዕኖ እያጠናከረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በቱርክዬ አንታሊያ በኮፕ 31 ጉባኤ ላይ እያደረገች ባለው ንቁ ተሳትፎና በከፈተችው መካነ ርዕይ የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿንና ሀገራዊ ትዕምርቶቿን ለዓለም እያስተዋወቀች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
በስምንት ዓመት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኝ የተከለችው ሀገራችን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በኮሪደር ልማት፣ በበጋ መስኖ፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባች መሆኑን ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መሪ ሚናን ከመወጣት ባለፈ አሁን ኮፕ 32ን አስተናጋጅ ሀገር ናት።
በኮፕ 31 ልምዷን እያጋራችና ከዝግጅቱ ልምድ እየቀሰመች እንግዶቿን በክብር ጠርታለች።
ከአንድ ዓመት በኋላ የምናስተናግደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ የልማት ተሞክሮዋን መሬት ላይ የምታሳይበት፣ ለአየር ንብረት ፍትሕና የልማት ፋይናንስ ገቢራዊነት የምትተጋበት፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፍ አጋርነት ያሉ ዕድሎችን የምታሰፋበት ታሪካዊ መድረክ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።