ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አደባባይ አሸናፊነቷን አጽንታ እንድትቀጥል አድርጓታል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት አደባባይ አሸናፊነቷን አጽንታ እንድትቀጥል ማድረጉን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው 4ኛው የ2026 የዓለም የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል።

ልዑኩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ኮሚሽነሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።

ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በዳካር በተካሄደው የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በውኃ ዋና፣ በቴኳንዶና በውሹ የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፋለች።

በውድድሩም አምስት የወርቅ እና ሦስት የብር በድምሩ ስምንት ሜዳሊያዎችን ማግኘቷን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህም ሀገራችን በዓለም አትሌቲክስ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ አንደኛ ደረጃን እንድትይዝ አስችሏል ብለዋል፡፡

ለተመዘገበው ድልና ስኬትም የተደረገው ቅድመ ዝግጅት እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ድጋፍ ወሳኝ ድርሻ እንደነበረው አመላክተዋል።

የመደመር መንግሥት ስፖርትን የሀገር ገጽታ መገንቢያ፣ የኢኮኖሚ ማሳደጊያ እና የሕዝቦችን አንድነት ማጠናከሪያ ትልቅ መሣሪያ አድርጎ እንደሚወስድ አስረድተዋል።

በዚህም አዳዲስ ስፖርተኞችንና ወጣት አትሌቶችን የማፍራት፣ አካዳሚዎችን የማጠናከር፣ የማዘውተሪያ ሥፍራዎችን የማስፋፋት፣ የማኅበራትን አሠራር ግልጽና ውጤታማ የማድረግ እንዲሁም የዘርፉን ድጋፍ የማሳደግ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አውስተዋል።

ለስፖርቱ ዘርፍ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት አደባባይ አሸናፊነቷን አጽንታ እንድትቀጥል ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የሴኔጋል ዳካር 2026 ተሳትፎ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቁመው፣ ውጤቱ ለቀጣይ ስፖርታዊ ድሎች ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በውድድሩ ዘጠኝ ወንዶችና ስምንት ሴቶች በድምሩ 17 ስፖርተኞች መሳተፋቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም