ቀጥታ፡

በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭት እንዳይባባስ የቅድመ መከላከል ስራ እየተከናወነ ነው-ጤና ቢሮው

ጋምቤላ ህዳር 5 /2019 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት እንዳይስፋፋ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ የወባ ተጋላጭነትን ለመከላከል በተከናወኑ ሥራዎች የስርጭት መጠኑን በ11 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ቢሮው ገልጿል።

በቢሮው የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ቴክ ዊሊያም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የወባ በሽታ ተጋላጭነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተከታታይና ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በክልሉ የክረምት መግቢያና መውጫን ተከትሎ ሊጨምር የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከል አምስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ጨምሮ በስምንት ወረዳዎች የፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በሁለት ወረዳዎች የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ስርጭት መካሄዱን ጠቁመው፤ በተከናወኑት ሥራዎችም የክልሉ የወባ ስርጭት መጠን ከቀዳሚዎቹ ዓመታት በ11 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ እየጣለ ካለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጋር ተያይዞ የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰትና የተገኘው ውጤት ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ በሁሉም አካባቢዎች የንቅናቄ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የጤና ተቋማት የፀረ-ወባ ፈዋሽ መድኃኒቶች በበቂ ሁኔታ መሰራጨታቸውንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

የጋምቤላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር እፁብ ወልዴ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት በወባ በሽታ ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት እየጣለ ካለው ዝናብ ጋር ተያይዞ የስርጭት መጠኑ እንዳይጨምር ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም ዶክተር እፁብ ተናግረዋል። 

በበሽታው ተጠቅተው ለሚመጡ ታካሚዎች በእንክብልም ሆነ በመርፌ የሚሰጡ በቂ የወባ መድኃኒቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም