ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከባሕር በር ውጪ ሆና ልትቀጥል አይገባም ሲሉ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ

ጭሮ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ከባሕር በር ውጪ ሆና መቀጠል አይገባትም ሲሉ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስገነዘቡ።

ኢትዮጵያ ላለፉት 35 ዓመታት የባሕር በር ባለቤትነቷን በሴራ ካጣች  በኋላ በጎረቤት አገራት ወደቦች ላይ ጥገኛ ሆና መቆየቷ በኢኮኖሚዋ፣ በንግድ ልውውጧና በቀጠናዊ ትስስሯ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ትምህርት መምህር አቶ ሰይፉ ደነቀ ለኢዜአ እንዳሉት ፤ ኢትዮጵያ ከጥንታዊ ሥልጣኔዋና ከገናና ታሪኳ ባለፈ በቀጠናው ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር፣ የኢኮኖሚ አቅምና ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ አንፃር ከባሕር በር ውጪ ሆና መቆየት አትችልም። 

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጠና የረጅም ዘመናት ፖለቲካዊና ታሪካዊ ሚና የነበራት በመሆኑ የባሕር በር ጉዳይ ከወቅታዊ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ባለፈ ከአገሪቱ የወደፊት ህልውና ጋር  የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት የባሕር በር ተደራሽነትን እንደ ዋነኛ ብሔራዊ አጀንዳ ማንሳቱ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባለፈ በቀጠናው ኢትጱያ ያላትን ተሳትፎና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማጠናከር ምትክ የማይገኝለት  መሆኑንም ገልጸዋል። 

በተለይም በቀጠናው የሰላም፣ የደኅንነትና የኢኮኖሚ ትስስር ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵ የምታበረክተውን ገንቢ ሚና ለማሳደግ የባሕር በር ተጠቃሚነት ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።

አንዳንድ ዜጎችም የፖለቲካ ዓላማቸውን ከአገራዊ ጥቅም በማስቀደም የባሕር በር ተደራሽነት ጥረቱን ሲቃወሙ ይስተዋላል ያሉት አቶ ሰይፉ፤ ከዚህ ይልቅ በጋራ መደገፍና በገንቢ ሀሳብ ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች የፖለቲካ አመለካከትን ሳይለዩ በሁሉም ዜጎች ዘንድ የጋራ አጀንዳ ሊሆኑ እንደሚገባም አክለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የሶሻል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ፍቃዱ ወርቁ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ቀይ ባሕር ለመመለስና ዘላቂ የባሕር በር ተደራሽነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ መስራት ተገቢነት ያለው  ነው ብለዋል።

ጉዳዩ የአንድ መንግሥት ወይም ፖለቲካን ብቻ የሚመለካት ሳይሆን የህልውናና የትውልድ ብሔራዊ ጥቅም መሆኑን አመልክተዋል። 

የባሕር በር ጉዳይ ከአገር ህልውና፣ ከኢኮኖሚ ደኅንነትና ከብሔራዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ቋሚ አጀንዳ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚገባም አንስተዋል።

በተለይም ምሁራን በምርምር፣ በጥናትና ሙያዊ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ለአገሪቱ የውጭ ግንኙነትና የልማት ጉዞ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል። 

ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር፣ በኢኮኖሚ ዕድገትና በቀጠናዊ አቅም እየጎለበተች ያለች አገር በመሆኗ የወደብ ተደራሽነት ፍላጎቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚሄድ አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል።

የባሕር በር ማግኘት የአገሪቱን የንግድ ወጪ ለመቀነስ፣ የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመሳብና የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።

መንግሥት የውጭ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም የታላቁ ኅዳሴ ግድብን ለፍጻሜ እንዳበቃ ሁሉ የቀይ ባሕርና የወደብ ባለቤትነት ጥያቄውን ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እንዲደግፉት ማድረጉ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥበብ መከተሉን ያሳያል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም