ቀጥታ፡

የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤን ማስተካከል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ሥርጭት ለመግታት መፍትሄ ነው -- የጤና ባለሙያዎች

ጋምቤላ፤ ሕዳር 5/2019 (ኤዜአ)፦ የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤን ማስተካከል እየጨመረ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት ለመግታት አንዱና ዋነኛው መፍትሔ መሆኑን በጋምቤላ ክልል የጤና ባለሙያዎች ገለጹ።

በክልሉ እንደ ደም ግፊት፣ ስኳርና የልብ ሕመም ባሉ በሽታዎች ተይዘው ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱም ተመላክቷል።

ቀደም ሲል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የአደጉ ሀገራት የጤና ችግር ብቻ ተደርገው ይወሰዱ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በታዳጊ ሀገራትም ከፍተኛ የጤና፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀውስ እያስከተሉ ይገኛሉ። 

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስመልክቶ ኢዜአ በጋምቤላ ከተማ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች እንዳሉት፣ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት ለመግታት የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤን ማስተካከል ወሳኝ ነው።   

ከጤና ባለሙያዎቹ መካከል የጋምቤላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሕክምና ክፍል ተጠሪ ዶክተር ንብረት አዳሙ እንዳሉት፣ ስኳርና የደም ግፊትን ጨምሮ ተላላፊ ባልሆኑ ሌሎች በሽታዎች የሚታመሙ ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ምንም እንኳ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተወሰነ ደረጃ በዘርና በዕድሜ የሚመጡ ቢሆንም አብዛኛው ሰው ላይ እየተከሰተ ያለው ከአመጋገብና አካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ አልኮል መጠጦችን፣ ጨዋማ ሥጋ እና ጨው የበዛባቸው ምግቦችን ከመቀነስ ባለፈ አካላዊ እንቅስቃሴን በማዘውተር ራሱን ከበሽታዎቩ መከላከል እንዳለበት መክረዋል።

የጋምቤላ ከተማ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ተክሌ ቢሻው በበኩላቸው የማህበረሰቡ በእግር የመጓዝ ባህል እየቀነሰ መምጣትና ለጤና ተስማሚ ምግቦችን ለይቶ አለመመገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መስፋፋት ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።

እንዲሁም የጤና ቅድመ ምርማራ የማድረግ ባህሉ አለመዳበር ሌላው ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ የእግር ጉዞን ማዘውተር፣ የአመጋገብ ዘይቤን ማስተካከልና የጤና ቅድመ ምርመራ በማድረግ በሽታዎችን ቀድሞ መከላከል ይቻላል ብለዋል።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከጤና ችግርነታቸው ባለፈ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስን ያስከትላሉ ያሉት ደግሞ ሌላው የጋምቤለ አጠቃላይ ሆስፒታል የጤና ባለሙያ እና የጋምቤላና አካባቢው የስኳር ሕሙማን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሳሙኤል ገለታ ናቸው።

በተለይም ስኳር፣ የደም ግፊትና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በወቅቱ መታከም ካልቻሉ ሌሎች የጎንዮሽ ጉዳቶችን ስለሚስከትሉ ሁሌም አስፋለጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብት አስገንዝበዋል።

የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ቴክ ዊሊያም በበኩላቸው እንደሉት፣ በየጊዜው እየጨመሩ የመጡትን ታላላፊ ያለሆኑ በሽታዎች ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በተለይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ ተላላፊ ባልሆኑ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች አስፋለጊውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን  ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም