ቀጥታ፡

ከምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ከ14 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማእከላዊ ገበያ ይቀርባል

ጭሮ፤ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ)፦ ከምስራቅ ኦሮሚያ ዞን በበጀት አመቱ ከ14 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ ጀማል ቃሲም ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ የቡና ምርትን በብዛትና በጥራት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው።

በበጀት ዓመቱ ከ14 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

እስካሁን ከ1 ሺህ 340 ቶን በላይ ቡና መቅረቡን ጠቅሰዋል።

የቡና ምርቱ ለገበያ እየቀረበ ያለው በ182 ቡና አቅራቢ ነጋዴዎችና በስድስት ዩኒየኖች አማካኝነት መሆኑን ተናግረዋል።

የቡና ዝግጅትና ግብይቱን ለማሳለጥ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ 46 የደረቅ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዞኑ የቡና ምርት ለገበያ የሚቀርበው በተደራጀ የአቅርቦት ሥርዓት በመሆኑ ለምርቱ ተደራሽነትና ለገበያ ትስስር መጠናከር የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቡና ግብይትና ዝውውር ሕጋዊ እንዲሆን ብሎም ጥራቱን ለማስጠበቅ በየደረጃው ያለው የቡና ምርት ጥራትና ግብይት ቁጥጥር ግብረ-ኃይል ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም