በነቀምቴ ከተማ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የከተማዋን ልማትና ዕድገት የማፋጠን ተግባራት እተከናወነ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ ከተማ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የከተማዋን ልማትና ዕድገት የማፋጠን ተግባራት እተከናወነ ይገኛል
ነቀምቴ፤ ህዳር 05/2019 (ኢዜአ)፦ በነቀምቴ ከተማ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን አሟጦ በመጠቀም የከተማዋን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አስታወቁ።
ከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች 950 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡም ተመላክቷል።
በከተማዋ ወቅታዊ የገቢ አሰባሰብንና ማዘጋጃቤታዊ ተግባራትን ጨምሮ በቅንጅት ሊሠሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ሰራተኞችና ከዘርፉ አመራሮች ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ገመዳ ተፈራ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የገቢ ምንጮችን በመለየትና በአግባቡ በማስተዳደር የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠን የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው።
«ግብር መክፈል ግዴታ ብቻ ሳይሆን የታማኝነት፣ የሥርዓትና የማኅበራዊ ኃላፊነት አካል ነው» ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ የከተማዋን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ በሚደረገው እንቅስቃሴ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
አያይዘውም የንግዱ ማኅበረሰብ የግብር ሕጎችን በመረዳት፣ የታክስ ግዴታዎችን የማወቅና የማሳወቅ ግዴታውን በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የውይይት መድረኩም በገቢ አሰባሰብ የሚታዩ ውስንነቶችን ለማቃለል፣ ሕገወጥ ንግድን ሥርዓት ማስያዝ ጨምሮ ሁሉም ነጋዴ በግብር ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፍ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የነቀምቴ ከተማ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስጋኑ ቶሎሳ በበኩላቸው፣ ማሕበረሰቡ በግብይት ወቅት ደረሰኝ ጠይቆ መቀበልና መስጠት የሰለጠነ ዜጋ መገለጫ መሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በከተማዋ ከ7 ሺህ በላይ ሕጋዊ ግብር ከፋዮች እንዳሉ ጠቁመው፤በተያዘው በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎቶች ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ነጋሽ አዲሱ እና አቶ ዱፌራ አበራ በበኩላቸው ፤ ሕጋዊ የገቢ ምንጮችን በመለየትና የግብር ከፋዮችን ግንዛቤ በማሳደግ የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የግብርና ታክስ አሰባሰብ ውጤታማ እንዲሆን የነጋዴዎችና የግብር ከፋዮች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ማንኛውም የዕቃና የአገልግሎት ሽያጭ በተገቢው ደረሰኝ እንዲከናወንና ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል እንዲዳብር እየሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል።