ኢትዮጵያ ከቱርኪዬ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቱርኪዬ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከቱርኪዬ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከቲአርቲ ወርልድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በኢትዮጵያ እና በቱርኪዬ መካከል ያለው ታሪካዊና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር ማሸጋገር ይገባል።
የቱርኪዬ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እያደገ ባለው ኢኮኖሚ ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመሪዎች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ለህዝብ ትስስር ላይ የቆመ ጠንካራ ወዳጅነት መሆኑን ገልጸዋል።
የቱርኪዬ ኩባንያዎች ከፍተኛ ልምድና ብቃት ባላቸው የአገልግሎት፣ የማኑፋክቸሪንግ እና የኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ በመሰማራት በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ባለው የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ ነው ያሉት።
ይህም ለሁለቱም ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ በቱርኪዬ አስተናጋጅነት እና በአውስትራሊያ የድርድር መሪነት እየተካሄደ በሚገኘው የኮፕ 31 ጉባኤ ስኬታማነት ሙሉ ድጋፏን እንደምትሰጥ ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ትብብር በሁለትዮሽ ንግድና ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።