የኮፕ-32 ጉባኤ የታዳጊ ሀገራትን የጋራ ድምፅና የመደራደር አቅም የሚያጎለብት ወሳኝ መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮፕ-32 ጉባኤ የታዳጊ ሀገራትን የጋራ ድምፅና የመደራደር አቅም የሚያጎለብት ወሳኝ መድረክ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የኮፕ 32 ጉባኤ የታዳጊ ሀገራትን የጋራ ድምፅና የመደራደር አቅም የሚያጎለብት ወሳኝ መድረክ መሆኑን የደቡባዊ ትብብር ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም ገለጹ።
ዋና ጸሐፊው ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ጉባኤው ታዳጊ ሀገራትን የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ አድርጎ የማየትን የተለመደ አካሄድ በመቀየር፣ ፖሊሲ አመንጪና ተጨባጭ መፍትሔ አቅራቢ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት የድርድር መድረክ ይሆናል።
የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ጉባኤውን ማስተናገዷ፣ ታዳጊ ሀገራት ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ከመግባታቸው በፊት የጋራ ጥቅማቸውን የሚያስከብር አንድ ወጥ አቋም እንዲይዙ ስትራቴጂካዊ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት ትብብር ከአየር ንብረት ፋይናንስ ባሻገር፣ ለታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ግብዓት የሚሆኑ ወሳኝ ማዕድናትን በሚያመርቱ ሀገራት መካከል ስትራቴጂካዊ ቅንጅት መፍጠር ላይ ማተኮር እንዳለበት አሳስበዋል።
ይህ ቅንጅት ማዕድን አምራች ሀገራት የወጪ ንግድ ቁጥጥራቸውን እንዲያጠናክሩ፣ የመደራደር አቅማቸውን እንዲያሳድጉና በዓለም አቀፉ የንጹሕ ኢነርጂ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ተገቢውን ድርሻ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
ታዳጊ ሀገራት ጥሬ ዕቃ እየላኩ የሶላር ፓኔሎችንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ የሚያስገቡበት ነባር የኢኮኖሚ ሞዴል መቀየር እንዳለበት የጠቆሙት ቢን ሙሳላም፣ ሀገራቱ በራሳቸው አቅም ቴክኖሎጂዎቹን በማምረት ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ምህዳራዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል።
የበለጸጉ ሀገራትም ለአየር ንብረት ፋይናንስ ከሚያደርጉት ድጋፍ ጎን ለጎን፣ በታዳጊ ሀገራት ውስጥ ማዕድናትን ወደ ታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ በሚቀይሩ ኢንዱስትሪዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
እ.አ. አ በ2027 በአዲስ አበባ በሚካሄደው 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32)፣ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ስምምነቶችን ከአፍሪካ የልማት የቅድሚያ ትኩረቶች ጋር በማስተሳሰር በምግብ ዋስትና፣ በንግድና በዘላቂ ኃይል ልማት ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።