የትግራይ ወጣቶች ለሰላም መስፈን ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል- የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ወጣቶች ለሰላም መስፈን ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል- የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦የትግራይ ወጣት የግዳጅ አፈሳንና የጦርነት አጀንዳን ባለመቀበል እስከ 800 ሺህ የሚደርሰው ወደ መሐል ሀገር መምጣቱን እና በቅርቡ ለተገኘው ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
በዚህም ለክልሉ ወጣቶች ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወላጆች ደግሞ ትውልድን ለእልቂት ከሚዳርግ የጅምላ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲወጡ መክረዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንደገለጹት፣ ታጣቂ ኃይሎች የኤርትራን የግዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት ተሞክሮ በመውሰድ በትግራይ ወጣቶች ላይ አፈሳን ሲያጠናክሩ፣ ወጣቱ ወደ አስመራ ከመሄድ ይልቅ ወደ እናት ሀገሩ መሐል ከተሞች መሰደድን መርጧል።
በዚህም እስከ 800 ሺሕ የሚደርስ ወጣት ወደ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ አሶሳ እና ጋምቤላ መሰራጨቱን ጠቅሰው፣ ወጣቱ ከጦርነቱና ከትሕነግ ጎን ባለመቆሙ ግጭቱ በአጭሩ እንዲቀለበስ ትልቅ ሚና መጫወቱን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በጫካ የቀሩት ጥቂት ተፈላጊ የቀድሞ አመራሮች እንጂ ወጣቶች አለመሆናቸውን አመላክተዋል።
ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት “ድርጅታችን” እና “ልጆቻችን ናቸው” በሚል የጅምላ መፈክር ክልሉን መቀየርና ቴክኖሎጂን መቀበል የሚችሉ ሐኪሞች፣ መሐንዲሶችና ዕድሜያቸው ያልደረሰ ታዳጊዎች በጦርነት እንዲያልቁ መደረጉን ፊልድ ማርሻሉ ብርሃኑ ጁላ ኮንነዋል።
በፖለቲካ ውስጥ በጅምላ ልጆቻችን የሚባል ቋንቋ የለም፤ ጥሩውን ማበረታታት፣ ክፉውን ደግሞ መቆጣትና ማስተካከል ይገባል በማለት ገልጸው፣ ለትግራይ ሕዝብ አንድን ድርጅት ብቻ መርጦ የመደበ የለም ብለዋል።
በቀጣይም የተሻለ ሐሳብ ያላቸው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉና ገና የሚፈጠሩም እንደሚኖሩ የጠቆሙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ ለዓመታት የትግራይን ሕዝብ በተለየ እንደ ተበዳይና ተገላይ አድርጎ የተገነባው ትርክት መልሶ ሕዝቡን እንደጎዳው አብራርተዋል።
ከዚህ አንጻር ከሃይማኖት አባቶች እስከ አርሶ አደሩ፣ ከወጣቶች እስከ ሀገር ሽማግሌዎች ድረስ ያለው ማኅበረሰብ ፍርሃትን በማስወገድ ጥፋትን በግልጽ እንዲያወግዝ እና ለዘላቂ ሰላም በጋራ እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።