ኮፕ 32 ኢትዮጵያ ተግባራዊ ተሞክሮዎቿን ለዓለም የምታቀርብበት እና ለአፍሪካ ድምጽ የምትሆንበት መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮፕ 32 ኢትዮጵያ ተግባራዊ ተሞክሮዎቿን ለዓለም የምታቀርብበት እና ለአፍሪካ ድምጽ የምትሆንበት መድረክ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ ኮፕ 32 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የወሰደቻቸውን እርምጃዎች ለዓለም የምታሳይበት እና ለአፍሪካ ድምጽ የምትሆንበት መድረክ እንደሚሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
31ኛው የተባበሩት መንግስት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) እየተካሄደ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከቲአርቲ ወርልድ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2017 ለምታስተናግደው 32ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ምቹ መደላድል ለመፍጠር፣ በኮፕ 31 ጉባኤ ስምምነቶች እንዲደረሱ በትኩረት እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
አፍሪካ ለዓለም አቀፍ የበካይ ጋዝ ልቀት የምታበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ መሆኗን አመልክተዋል።
ይህንን ለመቅረፍ ባደጉት ሀገራት የሚቀርቡ ቃል-ኪዳኖች ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ተግባራዊ እርምጃ ሲባል በአረንጓዴ ልማት፣ በአረንጓዴ መሰረተ-ልማት እና በኢንዱስትሪ ልማት ላይ የሚፈስ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ማለት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፣ ታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን የካፒታል ወጪ የሚሸፍኑበት አሰራር መፍጠር፣ የብድር ደረጃ ምዘና ፍትሃዊነት እንዲሁም ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ድርድሮች ቃል ከመግባት ባለፈ የሚተገበር የኢንቨስትመንት አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባ እና የፋይናንስ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል፣ በአረንጓዴ ትራንስፖርት እና በከተሞች ልማት የአየር ንብረት ጥበቃን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ማስተሳሰር እንደሚቻል በተግባር ማሳየቷን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ የሚካሄደው ኮፕ 32 ጉባኤም ኢትዮጵያ ይህንን ተግባራዊ ተሞክሮዋን ለዓለም የምታሳይበትና የአፍሪካን የልማትና የፋይናንስ ጥያቄዎች ወደ ተግባር የምትመራበት መድረክ እንደሚሆን ገልጸዋል።