በባሕር ዳር ከተማ የወባ በሽታ እንዳይስፋፋ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ የማጠናከር ስራ ተጀምሯል-ምክትል ከንቲባው - ኢዜአ አማርኛ
በባሕር ዳር ከተማ የወባ በሽታ እንዳይስፋፋ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ የማጠናከር ስራ ተጀምሯል-ምክትል ከንቲባው
ባህርዳር፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ) ፦ በባህር ዳር ከተማ እየታየ ካለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጋር ተያይዞ የወባ በሽታ እንዳይስፋፋ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎች መጠናከራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።
"የአርብ ጠንካራ እጆች ወባን ይገታሉ" በሚል መሪ ሃሳብ የወባ ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል የማህበረሰብ ንቅናቄ ስራ በግሽአባይ ክፍለ ከተማ ሰላም በር ቀበሌ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት፤ የወባ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ የቁጥጥር ስራዎች ተጀምረዋል።
የማህበረሰብ ንቅናቄ ስራዎች በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ቀበሌዎች እስከ መጪው ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት ።
ከዚህ ውስጥም በየሳምንቱ አርብ ለወባ ትንኝ መራቢያ አመች የሆኑና ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና የማዳፈን ስራ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።
"የወባ በሽታን ቀድመን መከላከል ካልቻልን የሰው ልጅ ህይወትን ይቀጥፋል" ያሉት አቶ አስሜ፤ ህብረተሰቡ ከአካባቢ ቁጥጥር ስራ ጎን ለጎን የአልጋ አጎበርን በአግባቡ ሊጠቀም ይገባል ነው ያለት።
የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌትነት የኔአባት በበኩላቸው፤ በከተማዋ እየጣለ ያለውን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ተከትሎ የወባ ስርጭት እንዳይስፋፋ የመከላከል ስራ ተጀምሯል።
ስርጭቱን ለመከላከል መላው ህብረተሰብ ለወባ ትንኝ መራቢያ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ተግባር ላይ አስተዋጽኦውን ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል።
በጽዳት ዘመቻው የተሳተፈችው ወይዘሪት ያለምጌጥ አድማሴ፤ በወባ በሽታ ምክንያት ለከፋ የጤና ችግር እንዳንጋለጥ የመከላከል ስራው መጀመሩ የሚያስደስት ነው ብላለች።
የከተማ አስተዳደሩ ዛሬ የአካባቢ ቁጥጥር ስራውን በማስጀመሩ ህብረተሰቡ ውሃ የሚያቆሩ ቦታዎችን እንዲያፀዳ በማድረጉ እራሱን ከበሽታ ለመጠበቅ እንዲችል ሰፊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገለፃለች።
ንቅናቄው "የወባ መራቢያ ቦታዎችን ለይተን በመከላከል ጤናችንን እንድንጠብቅ ያስችለናል" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ መለሰ ገላዋ ናቸው።
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በተጀመረው የአካባቢ ቁጥጥር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።