ቀጥታ፡

የጡት ወተት ባንክ ጨቅላ ሕጻናትን ከሞትና ከጤና እክሎች ለመታደግ እያገዘ ነው

ሀዋሳ ህዳር 04/2019 (ኢዜአ)--በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተጀመረው የጡት ወተት ባንክ ጨቅላ ሕጻናትን ከሞትና ከጤና እክሎች ለመታደግ እያገዘ መሆኑ ተገለጸ። 

የሀዋሳ የኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይድ ሆስፒታል በ2018 ሰኔ ወር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የጡት ወተት ባንክ አስመርቆ ወደሥራ ማስገባቱ የሚታወስ ነው።

የጡት ወተት ባንኩን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍፁም ወልደገብርኤል (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ባንኩ ጨቅላ ሕጻናትን ከሞትና ውስብስብ የጤና እክሎች ለመታደግ እያገዘ ነው።

በተለይ ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ጨቅላ ሕፃናት የእናታቸውን ጡት ወተት የማግኘት ዕድል ስለማይኖራቸው የደም መመረዝ፣ የአንጀት ቁስለትና ሌሎች የጤና እክሎች እንደሚገጥማቸው ገልጸው፣ ይህም ለሞት ይዳርጋቸዋል ብለዋል።

ባንኩ የእነዚህን ሕፃናት ሕይወት መታደግ ዓላማ  በማድረግ የተቋቋመ መሆኑንም ዶክተር ፍፁም ተናግረዋል። 

በአሁን ወቅት በሆስፒታሉ ተኝተው ለሚገኙ እንዲሁም ከሌሎች ጤና ተቋማት ለሚመጡ ጨቅላ ሕፃናት ባንኩ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡


ባንኩ ፍቃደኛ የሆኑ እናቶች ከልጃቸው የሚተርፈውን የጡት ወተት በልገሳ የሚሰጡበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸው፣ የተለገሰው የጡት ወተት የእናታቸውን ጡት ወተት ማግኘት ላልቻሉ ጨቅላ ሕጻናት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።  

ለዚህም ቅድሚያ የጤና ምርመራ እንደሚደረግ ገልጸው፣ የጡት ወተቱም ባክቴሪያና ቫይረስን የማስወገጃ ቴክኖሎጂ ሥርዐት ውስጥ አልፎ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለአገልግሎት እንዲውል ይደረጋል ብለዋል።


እንደ ዶክተር ፍጹም ገልጻ፣ አስፈላጊውን ሂደት አልፎ ደህንነቱ የተረጋገጠ ወተት በሚፈለገው የሙቀት መጠን በማቀዝቀዣ ማሽን ውስጥ አስከ ስድስት ወራት ሊቀመጥ ይችላል።  

የጡት ወተት ባንኩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ ኢትዮጵያን ዘጠነኛ ሀገር እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ ለልጃቸው የጡት ወተት ባንክ አገልግሎት ካገኙ እናቶች መካከል ወይዘሮ መቅደስ ብሩ በደም ግፊትና ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ምክንያት ልጃቸውን ያለቀኗ ለመውለድ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

በወቅቱ ከሕመማቸው በተጨማሪ ጡታቸው ወተት መስጠጥ ባለመጀመሩ ለልጃቸው ደህንነቱ የተጠበቀ ወተት ከባንኩ ማግኘቷንና ይህም ትልቅ እፎይታን እንደሰጣቸው ተናግራለች።


በአሁኑ ወቅት ለልጃቸው የራሳቸውን ጡት እያጠቡ ሲሆኑ ጤናዋም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ሌላዋ እናት ቤተልሔም ቡርጉዴ በበኩሏ ከዚህ ቀደም ያለጊዜዋ ለተወለደችው ልጃቸው የሌሎች እናቶች ጡት ወተት እንደተሰጣት አስታውሳ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተራዋ ከልጇ የተረፈውን ወተት እየለገሰች መሆኗን ተናግራለች፡፡

በቀጣይም ይህን መልካም ተግባር አጠናክራ እንደምትቀጠል ገልጻ፣ በጡት ወተት ባንኩ በሀኪሞች እርዳታ ልጇ ጤናዋ ተጠብቆ አሁን ላለችበት ደረጃ በመድረሱ ምስጋናዋን አቅርባለች።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጡት ወተት ባንክ በሰኔ ወር 2018 ዓ.ም ተመርቆ ወደሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም