ቀጥታ፡

ማዕከሉ ሀገራዊውን የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችንና የቴክኖሎጂ ድጋፎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ ነው

ሆለታ ህዳር 04/2019 (ኢዜአ) የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ሀገራዊውን የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችንና የቴክኖሎጂ ድጋፎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የቤተሰብን ሥርዓተ-ምግብ ለማሻሻል በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀርጾ እየተተገበረ የሚገኘው የ«ሌማት ትሩፋት» መርሃ-ግብር ፣ በተለይም በወተት፣ በእንቁላል፣ በዶሮ፣ በማርና በዓሣ ምርቶች ላይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ ነው።

ይህንን ሀገራዊ ግብ እውን ለማድረግ የግብርና ምርምር ተቋማት በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። 

በዚህም መሠረት የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ በተለይም በእንስሳት ሀብት ልማት፣ በተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያ ማዳቀል፣ በመኖ አዘገጃጀትና በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ያፈለቃቸውን የምርምር ውጤቶች ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ዘርፉን የማዘመን ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በማዕከሉ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ተመስገን ጀምበሬ  ለኢዜአ እንደ ገለጹት፤ የሆለታ ግብርና ምርምር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት መሰረት በማድረግ በወተት ላሞች፣ በበግና በፊየል እና በዶሮ ዝርያ ማሻሻያ ላይ እንዲሁም በእንስሳት መኖ እና ጤና አጠባበቅ ላይ ምርምር በማካሄድ ላይ ይገኛል። 

ማዕከሉ በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የቤተሰብ ሥርዓተ ምግብ እንዲሻሻልና የምግብ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ፣ የእንስሳትና የሰብል ምርቶችን በማጥናት፣ በማባዛትና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በማዕከሉ መካሄዱን አስታውሰው፤ በወቅቱም ዝርያቸው የተሻሻሉ 100 የወተት ላሞች ለአርሶ አደሩ መከፋፈላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ ማዕከሉ በቴክኖሎጂ ሽግገር እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የዘርፉ ዕቅዶችና ስትራቴጂዎች ላይ የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አክለዋል።

በማዕከሉ የእንስሳት ጤና ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ታምራት ስዩም በበኩላቸው፣ በእንስሳት ምርትና ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ በርካታ በሽታዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህ በሽታዎች በሰዎች ጤና ላይም ጉዳት ስለሚያስከትሉ ይህንን ለመከላከል ሰፊ ጥናትና ምርምር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የቀንድ ከብቶችና የወተት ላሞች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አንጡራ ሀብት በመደገፍ ረገድ ያላቸውን ሚና እንዳለው አንስተው፤  ለዚህ ወሳኝ ዘርፍም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በእንስሳት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ ባክቴሪያዎችን በመቆጣጠርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱን በማሻሻል የምርትና ምርታማነት ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

በማዕከሉ ድጋፍ የወተት ላሞችን በማርባት ውጤታማ ከሆኑት የአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ገረመው ወልደሰማያት በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል የወተት ላሞች እንዳልነበሯቸው አስታውሰዋል። 

በአሁኑ ወቅት ከማዕከሉ ባገኙት ሙያዊ ድጋፍና ምክር የወተት ምርት በማምረትና ለሆለታ ከተማ ነዋሪዎች በማቅረብ ኑሯቸውን ማሻሻላቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም