በአፋር ክልል ጤና ተቋማትን በቁሳቁስ በማደራጀት የአገልግሎት ጥራትን ይበልጥ ለማላቅ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል ጤና ተቋማትን በቁሳቁስ በማደራጀት የአገልግሎት ጥራትን ይበልጥ ለማላቅ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል
ሠመራ፣ ሕዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል ጤና ተቋማትን በቁሳቁስ በማደራጀት የአገልግሎት ጥራትን ይበልጥ ለማላቅና ተደራሽነትን ለማስፋት የሚከናወነስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በክልሉ በተለያዮ ዞኖች ለሚገኙ 61 ጤና ጣቢያዎች በፀሐይ ብርሃን ሐይል የሚሰሩና ለጤና አገልግሎት ሥራው አጋዥ የሆኑ ቁሶችን ዛሬ አከፋፍሏል።
የቢሮው ሀላፊ አቶ ያሲን ሀቢቦ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ የጤና ሥርአቱን በማዘመን ይበልጥ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።
በዛሬው እለትም በክልሉ በተለያዩ ዞኖች ለሚገኙ 61 ጤና ጣቢያዎች በፀሐይ ብርሃን ሐይል የሚሰሩና ለጤና አገልግሎት ሥራው አጋዥ የሆኑ ቁሶች መከፋፈላቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያከፋፈላቸው ቁሶች የሶላር ፓኔል ከነማስቀመጫው፣ ባትሪዎችና የሀይል ማመጣጠኛ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ያሲን፣ ቁሶቹ ጤና ተቋማቱ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ አጋዠ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ በኤሌክትሪክ ሀይል መጥፋት ምክንያት አገልግሎት እንዳይቋረጥና በማቀዝቀዣ የሚቀመጡ መድሃኒቶች ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ እንዲቆዮ በማድረግ በኩል ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም ጤና ተቋማትን በቁሳቁስ በማጠናከር አገልግሎታቸው ይበልጥ ጥራት ያለው እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋክል።
በቁሶቹ ርክክብ ሥነስርአት ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ባህል፣ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም እንዳሉት፣ የተሰራጩት ቁሶች በተለይ በኤሌክትሪክ ሀይል መቋረጥ የጤና አገልግሎት ላይ ችግር እንዳይከሰት የሚያግዙ ናቸው።
ከፀሐይ ብርሃን የሚገኝን ኀይል በመጠቀም በጤና ተቋማት ውስጥ ጥራት ያለውና በኤሌክትሪክ ሀይል እጦት ምክንያት ያልተቋራረጠ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በክልሉ ለእናቶችና ሕጻናት የሚሰጠውን ሕክምናና የክትባት አገልግሎት ቀልጣፋና የተመቻቸ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር የሚከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።