የመስኖ ፕሮጀክቱ በዓመት ሦስት ጊዜ እንድናመርት እድል ፈጥሮልናል- አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ ፕሮጀክቱ በዓመት ሦስት ጊዜ እንድናመርት እድል ፈጥሮልናል- አርሶ አደሮች
ደንቢያ ኢዜአ ኅዳር 4/2019 ዓ.ምበማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተገነባው የሳራቫ መስኖ ፕሮጀክት በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንዳስቻላቸው በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስተባባሪነት በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ዳህና ዋዋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታድሎ አስረስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በመስኖ ፕሮጀክቱ ለማልማት መቻሌ ተጠቃሚነቴን ለማሳደግ ረድቶኛል።
በዘንድሮው ዓመትም ከአንድ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት የእርሻ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ደምሌ በለጠ በበኩላቸው፤ በ2018 በጀት ዓመት በግማሽ ሄክታር መሬት ባለሙት ስንዴ 20 ኩንታል ምርት እንዳገኙ ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ተግባራዊ መደረግና ከግብርና ባለሙያዎች ጋር የሚደረገው የቅርብ ድጋፍ አርሶ አደሩ በመስኖ ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን እንዳስቻለው አንስተዋል።
የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማንአምቶ አገዘው፤ በተያዘው የበጋ ወቅት 9 ሺሕ 535 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ7 ሺሕ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ወደ ትግበራ መገባቱን ጠቅሰው፣ ከ270 ሺሕ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም አስታውቀዋል።
በዛሬው እለትም በዳህና ዋዋ ቀበሌ የሳራቫ ካናል ፕሮጀክት የበጋ መስኖ ስንዴ ክላስተር በ15 ሄክታር መሬት ላይ የማስጀመሪያ ሥራ ተከናውኗል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሲሳይ እንዳሉት፤ የበጋ መስኖ ልማት አቅምን በመጠቀም የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሠራ ነው።
ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስኬት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን የቅርብ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ ነው ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አስረሳው ደሴ ናቸው።
የሳራቫ መስኖ ፕሮጀክት የካናል ጥገና ሥራ በተደራጀ አግባብ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፕሮጀክቱን 4 ሺሕ ሄክታር የማልማት አቅም በተሟላ መንገድ ለመጠቀም እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።