የአዲስ አበባ የተቀናጀ መሰረተ ልማት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥርዓት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ የተቀናጀ መሰረተ ልማት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥርዓት ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ የተቀናጀ መሰረተ ልማት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥርዓት መፍጠሩን በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት የመሠረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ግዛቸው አይካ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አዲስ የተቀናጀ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥርዓት የምረቃና ማስተዋወቂያ መድረክ አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት የመሠረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ግዛቸው አይካ (ዶ/ር) ዲጂታል አሰራር ብክነትን፣ ብልሹ አሰራርንና የህዝብ እንግልትን በማስቀረት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል።
አዲስ አበባ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አሰራርን በመተግበር አገልግሎቶችን ግልጽ እና ቀልጣፋ በማድረግ የነዋሪዎችን እርካታ እያረጋገጠች እና ውጤት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ዛሬ በከተማው ትራንስፖርት ቢሮ የተጀመረው የተቀናጀ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥርዓት የዚሁ ሥራ አካል መሆኑን በመግለጽ የከተማው የትራንስፖርት ዘርፍ ስማርትና ቀልጣፋ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ተፈራ ሞላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ቴክኖሎጂን መጠቀም የዘመኑ ግዴታ ነው።
በከተማዋ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ መደገፋቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን እርካታ እያረጋገጡ መሆናቸውንም አንስተዋል።
አዲሱ የተቀናጀ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥርዓት ከዚህ ቀደም የነበረውን የስምሪትና ቁጥጥር ችግር በመቅረፍ፣ ሂደቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት።
ይህም ምቹ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር መደላድል በመፍጠር የትራንስፖርት አገልግሎቱ ፈጣን፣ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ ያደርጋል ብለዋል።
የለማው ሲስተም ህገወጥ ተሽከርካሪን ለመከታተል፣ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ያሉት ደግሞ ሲስተሙን ያበለጸገው የኤጂ ቴክኖሎጂ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ጌታሰው አበበ ናቸው።
ሲስተሙ የተሽከርካሪ ምደባ፣ የተሽከርካሪ ተቆጣጣሪ ምደባ፣ የተሽከርካሪ አቴንዳንስ፣ የተገልጋይ ጥቆማ፣ የተጠሪ ተቋማት ሪፖርት እና ዕለታዊ ክስተት ሪፖርት ይዘቶችን እንደሚያካትት ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ታክሲ ማህበር መሪ አቶ ጌቱ ተስፋዬ የበለጸገው ሲስተም ለረዥም ጊዜ ስንፈልገው የነበረና በተቆጣጣሪና በታክሲ ሾፌር መካከል ይከሰት የነበረውን አለመግባባት ይፈታል ብለዋል።
የአደይ አበባ ብዙሃን ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር አባል ብርሃኔ የኋላሸት በበኩላቸው ሲስተሙ የእጅ ንክኪን በማስቀረት ዲጂታል ሥርዓትን እንደሚያሰፍን ተናግረዋል።