የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የልማትና የደህንነት ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የልማትና የደህንነት ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባለው ቀጣና የባሕር ላይ ደኅንነትን ለማስጠበቅና ሽብርተኝነትን በማጥፋት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የፈረንሳይ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ዳሜየን ሲፕሪክ ገለጹ።
የፈረንሳይ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ዳሜይን ሲፕሪክ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የቀጣናው ኃያል አቅም በመሆኗ በዓለም ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና አላት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት በቀጣናውን ሰላምና ደህንነትን በማስፈን ሽብርተኝነትን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጥያቄ ቅቡልነት ያለው የልማትና የደህንነት ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና መረጋጋት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምታቀርበው የባሕር በር ፍላጎት መልክዓ ምድራዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድር ከቀይ ባህር ያላት ቅርበትና ከአካባቢው ወደቦች ጋር ያላት ታሪካዊ ትስስር ሉዓላዊ የባህር በር ለማግኘት ለምታደርገው ጥረት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የቀይ ባህርና የባብ ኤል መንደብ ሰርጥ ለአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ ስትራቴጂያዊ ስፍራዎች ናቸው ያሉት ወታደራዊ አታሼው፤ ከቀጣናው ያለፈ ሰፊ አንድምታ እንዳለው ገልጸዋል።
በእነዚህ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባላቸው አካባቢዎች የሚከሰቱ ለውጦች በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ቅቡልነት ያለው አበርክቶ እንዳላት በማንሳት፤ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባት ገልጸዋል።