ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ብዝኃነትና አንድነት አስተሳስሮ ለማራመድ ትልቅ መሠረት ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ብዝኃነትና አንድነት አስተሳስሮ ለማራመድ ትልቅ መሠረት መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ገለጹ። 

በመደመር እሳቤ ላይ የተመሠረተ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን የማጠናከር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።

የመደመር መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ዘርፍን እንደ ትልቅ ሀገራዊ ሀብት በመውሰድ፣ የኢትዮጵያን ብዝኃነትና ሕብረ-ብሔራዊ ትስስር በማጠናከር ላይ ይገኛል። 

በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና መንፈሳዊ ስፍራዎችን በማልማት እንዲሁም ቅርሶችን በመንከባከብ የሀገራችንን ገጽታ ከፍ የማድረግ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ 

በዘርፉ የተከናወኑ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችና መዳረሻዎችን የማስዋብ ሥራዎችም ሕዝቦች በአብሮነት እንዲያድጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን እነዚህ ሁለገብ ጥረቶች ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ ቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ተጠቃሚነት እያሳደጉት ይገኛሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የመደመር ፍልስፍና የኢትዮጵያን ብዝኃነት፣ የባህል እና የማንነት መገለጫዎች መሠረት አድርጎ የተነሳ አጠቃላይ ሀገር በቀል እሳቤ መሆኑን ገልጸዋል። 

የመደመር ፍልስፍናው የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ፣ የሕዝቦቿን ማንነትና የዕለት ተዕለት አኗኗር ሥርዓት የሚመጥን አጠቃላይ መርህ እንደሆነም ተናግረዋል።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የራሱን የኑሮ እሳቤ ይዞ፣ ከባህል ድምርና ጥርቅም ጋር በታላቋ ሀገር ውስጥ አብሮ የመኖርና የመከባበር እሴቶችን እንደሚያጎለብትም ጠቁመዋል።

የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ብዝኃነትና መልከ-ብዙነት ሙሉ በሙሉ የሚቀበልና ይህንኑ መሠረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አንዳችን የሌላኛችንን ጥንካሬ እያጎላን፣ ክፍተት እየሞላንና እየተጋገዝን መኖር አለብን በሚለው አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ትልቅ ፍልስፍና መሆኑን አብራርተዋል።

መንግሥት ከሚመራባቸው ዘርፎች አንዱ የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን ገልጸው፤ በብራንዲንግ፣ በባህልና በኪነ-ጥበብ ዘርፎች ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

የብዝኃነት እሴት ለወደፊት የሥልጣኔ ጉዞ እንደ ጉልበትና አጋዥ ሆኖ ለሰላም፣ ለብልፅግና እንዲሁም ለነገ ልጆች የኑሮ ዋስትና በሚሰጥ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በመንግሥት ሕዝቦች በቋንቋቸውና በባህላቸው እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ሰፊ አውድ መፈጠር መጀመሩን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሀብት የሆኑትን ቋንቋዎች፣ ባህሎችና እምነቶች እንደ ውብ የአብሮነት አበባ በመቁጠር በቅንጅት  እና በማዕከላዊ መንገድ ማቀንቀን ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያን ብዝኃነትና አንድነት አስተሳሰቦች አጣጥሞ በመያዝ ጠንካራ፣ የበለፀገችና ለሁሉም ዜጎች ምቹ የሆነች ሀገር ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም