በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀናጀ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ስርዓት የትራንስፖርት አገልግሎቱን በማሳለጥ የከተማውን ንግድና ማህበራዊ ግንኙነት ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀናጀ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ስርዓት የትራንስፖርት አገልግሎቱን በማሳለጥ የከተማውን ንግድና ማህበራዊ ግንኙነት ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ በቴክኖሎጂ የተደገፈው የተቀናጀ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ስርዓት የከተማውን የትራንስፖርት ስምሪት በማሳለጥ፣ የንግድ እንቅስቃሴውንና ማህበራዊ ግንኙነቱን የሚያጠናክር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው የተቀናጀ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ስርዓት የምረቃና ማስተዋወቂያ መድረክ አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ተፈራ ሞላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ቴክኖሎጂን መጠቀም የዘመኑ ግዴታ ነው።
በከተማዋ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ መደገፋቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን እርካታ እያረጋገጡ መሆናቸውንም አንስተዋል።
አዲሱ የተቀናጀ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ስርዓት ከዚህ ቀደም የነበረውን የስምሪትና ቁጥጥር ችግር በመቅረፍ፣ ሂደቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም በከተማዋ የትራንስፖርት ስምሪትን በማቀላጠፍና ምቹ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር መደላድል በመፍጠር ሀገራችን የያዘችውን የብልጽግና ራዕይ እውን ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
ስርዓቱ የከተማውን የንግድ ስርዓት በማፋጠን ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር ከመሆኑም ባለፈ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ፈጣን፣ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ በመድረኩ ተመላክቷል።